The battle of Adwa

የዐድዋ ድል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት አስተላለፉ

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 2, 2020)፦ በዛሬው ዕለት የዐድዋ 124ኛ ዓመት የድል በዓል ይከበራል። የዛሬ 124 ዓመት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዐድዋ ላይ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የቃጣውን የጣሊያንን ጦር ያሸነፉበትና የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ሕልሙን ያኮላሹባት ዕለት ነች።

ዐድዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ብቻ ሳይኾን የጥቁር ሕዝቦች ለነፃነት ላደረጉት ትግል የመጀመሪያውን ሻማ የለኮሰ የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል እንደኾነ ይታወቃል። ዐድዋ የታላቅ ሕዝቦች ታላቅ ድል ሲሆን፣ ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓውያንን ያሸነፉበት መድረክ ነው።

ይህንን ታላቅ በዓል አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዐድዋ ድል መታሰቢያን አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል። በዚሁ መልእክታቸው ላይ “የትናንት እናቶቻችንንና አባቶቻችንን ድል ዛሬ እንዳከበርነው ሁሉ የእኛንም ድል ነገ ልጆቻችን ያከብሩታል። እነርሱ የቅኝ ግዛትን ቀንበር ሰብረው ነው። እኛ ደግሞ የድህነትን ቀንበር እንሰብራለን። እነርሱ ነፃ አገር ፈጥረዋል፤ እኛ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ አገር እንፈጥራለን። እነርሱ በመደመር ተጉዘው ድል አስገኝተዋል። እኛም በመደመር ተጉዘን የብልጽግናን ድል እናስገኛለን።” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የዐድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን በተመለከተ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው፤ (ኢዛ)

እንኳን ለ124ኛው የዐድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!

ዐድዋ በየትውልዱ እየተመነዘረ ለብልጽግና ጉዟችን ልንጠቀምበት የምንችለው ትልቅ ሀብታችን ነው። ዐድዋ ኢትዮጵያዊያን አንድም ብዙም መኾናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው። በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነት የየራሳችን ማንነት አለን። ይህ ማንነታችን በአገራችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ታግለናል፣ እንታገላለን። ከዚህ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ያሰኘን አንድነትም አለን።

ጣሊያኖች ወደ ዐድዋ ሲመጡ የታያቸው ልዩነታችን ነው። በልዩነታችን ላይ ሠርተው ኢትዮጵያውያንን በማዳከም ቅኝ ግዛትን ሊጭኑብን አስበው ነበር። የኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጸጋዎች መከፋፈያ የሚሆኑ መስሏቸው በተለያየ መንገድ ሞክረው ነበር። ወደ ዐድዋ ሲመጡ ግን ያሰቡትን አላገኙም። ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ በነፃነታቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆኑን አሳዩ። ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጸጋ እንጂ መለያየት እንደሌላቸው ዐድዋ አሳያቸው። ኢትዮጵያውያን ሕብራዊ አንድነት እንዳላቸው ዐድዋ መሰከረ።

ልዩ ልዩ ጸጋዎቻችንን የመለያያ ምክንያት የማድረግ ዘመቻ ፈጽሞ እንደማይሳካ ዐድዋ ህያው ምስክር ነው። ኢትዮጵያውያን በዐድዋ ዘመቻ ዋዜማ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ነበሯቸው። ከወቅቱ መሪዎች ጋር በሁሉም ነገር የሚስማሙ አልነበሩም። የዘመኑ አስተዳደር ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አልነበረም። እነዚህን አገራዊ ችግሮች አቀጣጥለው አገር የማዳከሚያ መሳሪያ ለማድረግ ጣሊያኖች ሞክረዋል። ቁስሉን ለማዳን ሳይሆን በቁስሉ ለማስለቀስ ጥረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ችግራችንን እንፈታለን፤ አገራችንን እንጠብቃለን ብለው አልተቀበሉትም።

ጥያቄዎች ሁሉ የሚመለሱት አገር ስትኖር መሆኑን ኢትዮጵያውያን ያውቁ ነበር። ኢትዮጵያዊን ለቁንጫ ብለው ቤት የሚያቃጥሉ፣ ለአረም ሲሉ ማሳውን የሚያጠፉ አልነበሩም።

ኢትዮጵያዊን አገራቸውን በተመለከተ ዘላቂ መርህ አላቸው። ዋልታና ማገሩን እጠብቃለሁ፤ ውስጡንም አጸዳለሁ የሚል፣ ቤቱ ቤት ሆኖ እንዲኖር ዋልታና ማገሩን ማጥበቅ ያስፈልጋል። ቤቱን ለማጽዳት መጀመሪያ ቤቱ ቤት መሆን አለበት። ቤቱ በሌለበት የቤት ጽዳት አይኖርም። ቤቱ ግን ሊቆሽሽ ወይም ተባይ ሊያፈራ ይችላል። ቤቱን እያጠበቅን እያጸናን ውስጡን ደግሞ እናጸዳለን።

ዐድዋ ሌላም ትምህርት ሰጥቶናል። ችግሮቻችንን እንዴት ማየት እንዳለብን። አጼ ምኒልክ ለዐድዋ ዘማቾች ለዘመኑ ችግር በቂ ዝግጀት አድርገው ነበር። ያዘጋጇቸው መድፎች ከጣሊያን መድፎች የተሻሉ ነበሩ።

ጣልያን ወታደሮቹን ካንቀሳቀሰበት ዓቅም በላይ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ ችለዋል። የት ቦታ፣ እንዴት ጠላቶቻቸውን ገጥመው ሊያሸንፉት እንደሚችሉ ዓቅደዋል። የዐድዋ ድል የዚህ የላቀ ዝግጅት ውጤት ነው።

ከአርባ አመታት በኋላ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ልንቋቋመው ያልቻልነው በዐድዋ ዘመቻ ያደረግነውን ነገ ተኮር ዝግጅት ስላላደረግን ነው።

ጣሊያን በአየር ሲመጣ በመሬት ገጠምነው። ጣሊያን የምድር ላይ ዘመቻዎቹን አዘምኖ ሲመጣ እኛ ያለንን ይዘን ጠበቅነው ከዘመኑ ቀድመን አልተገኘንም።

ዛሬ ከትላንት የተለየን መኾናችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ስልጣኔ ማለት ከነገ መቅደም ነው። ነገ ከሚመጣ ችግር በልጦ መገኘት ነው። ከዐድዋ የምንማረው አንዱ ትልቁ ትምህርት ይህ ነው። ትላንት ለገጠመን ችግር መፍትሄ መስጠት ችሎታ ነው። ዛሬ ለሚገጥመን ችግር መፍትሄ ማስቀመጥ ብልሃት ነው። ወደ ፊት ከሚመጣ ችግር በልጦ መገኘት ግን ጥበብ ነው።

የዐድዋ ዘመቻ የጦርነት ዘመቻ ብቻ አልነበረም የቴክልኖሎጂ ዘመቻ ፤ የዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ የትዕግሥት ዘመቻ፣ የፖለቲካ ዘመቻ፣ የሎጂስቲክ ዘመቻ፣ የፍቅርና የይቅርታ ዘመቻም ጭምር ነበር። በዘመኑ የተሻሉ መሳሪያዎችን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለዝግጅት ጊዜ ለማግኘት እንዲቻል የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቷል። ችግርን በትክክለኛው ጊዜና ሁኔታ ለመግጠም ሲባል በፈታኝ ትዕግስት ውስጥ ታልፏል። ለዚያ ሁሉ ሰራዊት የሚሆን ስንቅና ትጥቅ ለማዘጋጀት ሕዝቡን አንቀሳቅሰዋል። ውስጣዊ ቅራኔዎች አገራዊ አደጋ እንዳያስከትሉ የዕርቅና የመቻቻል ስራዎች ተሰርተዋል።

ዛሬም እንደ አገር የገጠመንን ችግር ለመፍታት የዐድዋ ዘማቾች የተጠቀሙበትን ዘርፈ ብዙ መፍትሄዎች መጠቀም አለብን። ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ዲፕሎማሲ ትግል ማድርግ፣ በትግዕስት ጊዜ መስጠት፣ የፖለቲካ መፍትሄዎችን መስጠት፣ አቅም ማጠራቀም፣ በፍቅርና በይቅርታ መንገድ መጓዝ፣ ሌሎችም ያስፈልጉናል።

የዐድዋ ዘመቻ ድል እንዴት ማጠናቀቅ እንደሚቻል ያስተማረ ትልቅ ታሪካችን ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የመጣባቸውን ወራሪ መክተዋል። መክተዋል ብቻ ሳይሆን አሳፍረው መልሰዋል።

ነገር ግን የውጭ ጠላታቸውን ድል ያደረጉበትን አቅም የራሳቸውን ጉዳይ ለመፍታት አላዋሉትም። አንድ ታላቅ አገራዊ ድል ካገኘን በኋላ ውሰጣዊ ጥንካሬያችንን በድላችን ልክ ለማድርግ ካልሰራን ድላችንን የሚያሳጣን እድል ሊገጥመን ይችል ይሆናል። ለምን አሸነፍን? ያሸነፍንበት ሚስጥር ለውስጣዊ የአገር ግንባታ እንዴት እንጠቀምበት? የዛሬውን ጠላት አሸንፈን ነገር ግን ኢትዮጵያን ነገ ከሚመጣው ጠላት የተሻለች አድርገን እንዴት እናቆያት?

እነዚህን ጉዳዮች አለማየት ከዐድዋ ድል ዐርባ ዓመት በኋላ በማይጨው ዘመቻ የገጠመንን እንዲገጥመን መፍረድ ነው። ያ እንዲሆን ዛሬ ፈጽሞ አንፈቅድም። በዐድዋ ድል የተነሳ ብዙ ሕዝቦች ሮጠው ቀድመውናል። የተሻለ አገረ መንግሥት ገንብተዋል፡ የተሻለ ብሄረ መንግሥት አዳብረዋል። ዴሞክራሲያቸውን፣ የፍትሕ ሥርዓታቸውንና ኢኮኖሚያቸውን አዘምነዋል። ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ሲቆረጥ ለምን ዝም እንላለን?

የመደመር ጎዳና ኢትዮጵያ የዐድዋ ድሏን በሚመጥን ደረጃ እንድትጓዝ የተገነባ መንገድ ነው። ለዐድዋ ድላችን የሚመጥነው የኢትዮጵያ ከፍታ ብልጽግና ነው። እኛ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጣን የዐድዋ ዘማቾች ነን። አንድ ሆነን ጠላታችንን ተዋግተን ድል እንዳደረግነው ሁሉ አንድ ሆነን አገር እንገነባለን። አንድ ሆነን አገራችንን ወደ ብልጽግና እናደርሳለን።

የትናንት እናቶቻችንንና አባቶቻችንን ድል ዛሬ እንዳከበርነው ሁሉ የእኛንም ድል ነገ ልጆቻችን ያከብሩታል። እነርሱ የቅኝ ግዛትን ቀንበር ሰብረው ነው። እኛ ደግሞ የድህነትን ቀንበር እንሰብራለን። እነርሱ ነፃ አገር ፈጥረዋል፤ እኛ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ አገር እንፈጥራለን። እነርሱ በመደመር ተጉዘው ድል አስገኝተዋል። እኛም በመደመር ተጉዘን የብልጽግናን ድል እናስገኛለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራ እና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ