(ከየካቲት 8/1929 - የካቲት 17/1929 ዓ.ም)

ሰሎሞን ተሰማ ጂ.

በመስከረም 1927 ዓ.ም የወጣው Detroit Times — (Sept. 22, 1935, p. 3) መጽሔት ከአንድ ታላቅ ሳይቲስትና የፈጠራ ባለሙያ ጋር የኢትዮጵያንና የጣሊያንን ወረራ አስመልክቶ ቃለ-ምልልስ አድርጎ ነበር።


Nikola Tesla Tells How He'd Defend Ethiopia Against Italian Invasion (www.tesla.hu/tesla/articles/19350922.doc) በቃለ-ምልልሱም ላይ ጋዜጠኛው ዶ/ር ኒኮላ ቴስላን እንዲህ ብሎ ጠየቀው፤ "ካለፈው የካቲት 1935 (እ.አ.አ) ጀምሮ ኢጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል ወራለች። አንተ ንጉሠ ነገሥቱን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?" መላሹ ዶ/ር ኒኮላ ቴስላም ትንሽ ጊዜ ትክዝ ካለ በኋላ፤ "እኔ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ብሆን ኖሮ፣ በከተሞች አካባቢ ያለውን ሕዝብ በመላ ወደገጠርና ወደዱር ገደሉ እንዲሄዱ አደርገዋለሁ። ሕዝቡ ከከተሞች ወጥቶ ወደገጠራማ ቦታዎች እንዲያፈገፍግ አዘዋለሁ።" ጋዜጠኛው ጣልቃ ገባ፤ "ለምን?" አለው። ቴስላም ቀጠለ፤ "የአሁኗ ኢጣሊያ መሪዎች ክፉኛ ማስተዋል የጎደላቸው ጣሊያኖች ናቸው። የፋሺዝም ርዕዮት-ዓለም እውር አድርጓቸዋል። ስለሆነም ከፍተኛ ጭፍጨፋ በከተሞች በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እንደሚፈጽሙ ይታየኛል። ስለሆነም ሕዝቡ ከከተሞች ወጥቶ ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ወፍለስ አለበት።" ጋዜጠኛው ግራ ገባው፤ ጥያቄዎቹን አዥጎደጎደ፤ "ኢጣሊያ ትልቅ አገርና በሥልጣኔም ቢሆን ከኢትዮጵያ የተሻለች ሆና ሳለ እንዴት እንደዚህ ያለ የአረመኔዎች ግፍ ልትፈጽም ትችላለች ብለህ ታስባለህ?"

 

ሊቁ ኒኮላ ቴስላ ረጋ ባለ አንደበት መናገሩን ቀጠለ፤ "እንዳልከውና እናንተ ጋዜጠኞቹ እንደምትደሰኩሩት አይደለም። ኢጣሊያ ከአትዮጵያ የበለጠ ሥልጣኔ የላትም፤ ነገር ግን ቴክኖሎጂውና በዘመናት ውስጥ በጦርነት ምርኮና ዘረፋ ያከማቸችው ሀብት አላት። ኢትዮጵያ ግን ነፃነቷን ተከላካይ አገር አንጂ ወራሪ ሃይል ሆናም ስለማታውቅ በዝርፊያ የተከማቸ ሀብት የላትም። በሥልጣኔ በኩል ካየኸው ግን ኢትዮጵያ ጁሊየስ ቄሳር ከመነሳቱና የዛሬዋ ኢጣሊያ ከመፈጠራ በፊት ብዙ ሺህ አመታት በፊት የሰለጠነች አገር ናት። እናንተ ጋዜጠኞቹና የፋሺስት ፕሮፓጋንዲስቶቹ እንደምታወሩት አይደለም።" ቴስላ ትንሽ ቆም አለ። ወዲያውም ቀጠል አድርጎ፤ "ይኼንን ስልህ ኢጣሊያ የእነሴኔካ፣ የነጆቫኒ ቦካሺዎ፣ የነፔትራርች፣ የነሊዎናርዶ ዳቬንቺ፣ የነሚካኤል አንጄሎና የነጋሊሊዮ ጋሊሊ አገር መሆኗን እያወቅኩ ነው። ዛሬ ኢጣሊያ (በ1920ዎቹ ማለቱ ነው) ያ የከያኒነትና የተመራማሪነት መንፈስ ከኢጣሊያ ጠፍቶ፣ በፋሺዝምና በጭፍን ካቶሊካዊነት ልጓም የሚፈረጥጡ ልጆች አገር ሆናለች።" ሲል ለረጅም ደቂቃዎች በትካዜ ነጎደ።


ቴስላ የፈራውና የገመተው የአስተዋይነት መጥፋትና የጭፍንነት መንገሥ እውን ሆኖ ለመታየት ስድስት ወራት ብቻ ተቆጠሩ። ከየካቲት 12-14/1929 ዓ.ም ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ማመዛዘን የማይችሉት ፋሺስቶች በኢትዮጵያውያን ላይ አለን እያሉ ከሚኮፈሱበትና ከሚመጻደቁበት "ሥልጣኔያቸው" ጋር አብሮ የማይኼድ አረማዊ ሥራ ሠሩ። ፋሺዝምም ሆነ ኮትኩቶና በሮማ አደባባይ መርቆ ሂዱ ኢትዮጵያን ውረሩ ብሎ የላካቸው ካቶሊክኢዝም ምን ያህል "ሥልጡን" እንደነበሩ በገሀድ አሳዩ። (አፈር ድሜ ኮትኳችነት-እቴ!) በተጨማሪም፣ የፋሺዝምን ዘረኝነትና ዘላለማዊ ቁስሉን ለዓለም አስመሰከሩ። ከ76 ዓመታት በኋላ ቁስሉ የጠገገኛ የዳነ ቢመስልም እንኳን፣ ጠባሳውን ስድስት ኪሎ በሚገኘው የየካቲት 12 ሰማዕታት ሃውልት አማካይነት ሕዝብ ዕለት በዕለት ያየዋል። ምን ያህሉ ምስጢሩ ገብቶት፣ የቁስሉ ሕመምና የጠባሳው ግዝፈት እንደሚያንገበግበው ባላውቅም፤ ገሚሱ በእግር፣ ሌላው በመኪና እግር (ጎማ) ሲያልፍና ሲያገድም ያየዋል። "ምን ያሕሉስ እነዚያን የጽልመትና የመከራ ቀናት ከአምሳለ-ሃውልቱ ተሻግሮ ያስተውላቸዋል?" የሚለውን መገመቱ ግን ይከብዳል። (በነገራችን ላይ፣ ቤላ የሚገኘው የኢጣሊያ ኤምባሲ ዲፕሎማቲክ አባላት በዚህ ሃውልት በኩል ለማለፍ ጨርሶ አይዳዱም። በራሳቸው ወጪ ባሰሩትና ከሕሊናቸው ለመሸሽ ብለው በዘየዱት አቋራጭ መንገዳቸው፣ በጀርመን ኤምባሲ በኩል ይገባሉ-ይወጣሉ እንጂ የቤላ ስድስት ኪሎ መንገድን ለመጠቀም አይሹም። ልብ ያለው ልብ ይበል!)

 

የየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በይፋ ማክበር የተጀመረው በ1934 ዓ.ም ነው። በዚያን ጊዜ የነረውም ሃውልት፣ ይህ ዛሬ ትከሻውን አሳብጦ፣ ደረቱን ገልብጦ ቆሞ የምናው ሃውልት አልነበረም የተተከለው። ያኛው ሃውልት እስከ 21ኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን (ማለትም፣ እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ ለመታሰቢያነት ሲያገለግል ቆየ በኋላ፣ በ22ተኛው የሰማዕታት መታሰቢያ ቀን/ዕለት ይኼኛው የመታሰቢያ ሃውልት በዩጎዝላቪያ መንግሥት ርዳታ ("በማሻል ዴኒስ ቲቶ እርዳታ አማካይነት" ማለቱ ሳይሻል አይቀርም) በ1951 ዓ.ም በይፋ ተመረቀ። ለዚሁ የሃውልት ምረቃና ለተለያዩ የጉብኝትና የወዳጅነት ሥራዎችም ሲሉ የዩጎዝላቪያው ፕ/ት ማርሻል ዴኒስ ቲቶ ከነባለቤታቸው፣ ከጥር 25 ቀን 1951 ዓ.ም እስከ የካቲት 6 ቀን 1951 ዓ.ም ድረስ ይፋ ጉብኝት አድርገው ነበር (አዲስ ዘመን፣ የካቲት 7/1951 ዓ.ም፣ ገጽ 1)። ይህም ጉብኝታቸው ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ጉብኝት ነበር። ቀዳሚው ጉብኝት ከታኅሣሥና በጥር 1948 ዓ.ም የተደረገ ይፋ የ14 ቀናት ጉብኝት ነበር። ምናልባትም በዚህ ወቅት ሳይሆን አይቀርም ስለየካቲት 12ቱ የሰማዕታት ሃውልት ሥራ/ትብብር የተጠየቁት። በዚህም መሠረት የሥነ-ሃውልትና የቅርጻ-ቅርጽ ባለሙያዎች ከዩጎዝላቪያ መጥተው ይህ ዛሬ የምናየው ሃውልት በመጀመሪያው ሃውልት ስፍራ ላይ ተተካ።

 

ከየካቲት 12ቱ የሃውልት አሠራርና ታሪክ ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ወጥተን፣ በቀጥታ ወደ የካቲት 1929 ዓ.ም እንለፍ። የካቲት 1929 ዓመተ ምህረትን ያህል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የመከራና የጽልመት ወራት ኖሮ አያውቁም። በጣም የሚገርመው፣ በዚሁ በወርኃ የካቲት 1888 ዓመተ ምህረትም ከሰባ ሺህ በላይ ወገኖቻችንን መሥዋዕት አድርገናል። ግፈኛው የንጉሥ ኡምቤርቶ ጦር፣ በጄኔራል ባራቴሪ እየተመራ ሃይማኖት ሊቀለብስ፣ መሬት ሊቆርስ፣ ነፃነታችንን ሊገስ መጥቶ ማጭድና ጎራዴ፣ ጦርና ጋሻ የያዙትን ወኔያም አያቶቻችንንና ቅድመ-አያቶቻችንን በመድፍና በዘመኑ መሳሪያዎች ፈጃቸው። ከአርባ አንድ ዓመታት በኋላ ተመልሶ ለወረራ የመጣው በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራው የፋሺስትም ጦር፣ ከየካቲት 12 ቀን እስከ የካቲት 14 ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ከሠላሳ ሺህ በላይ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያንን ፈጃቸው። ጣሊያን ብቻውን አልነበረም፤ የእኛም ሰዎች አጅ አለበት። ለጣሊያን ጭፍጨፋዎች ተባባሪ ሆነን ጭፍጨፋውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አግዘናል። ("እኛ" የምለው "እኛ የኢትዮጵያዊነትን ጽድቅና እውነት" ችላ ብለን ለጣሊያን በባንዳነትና በጭፍራነት ወይም በአስካሪነት ተሰልፈው የነበሩትን ኤርትራውያን ምንደኞችም አካትቼ ነው። "እኛ" ስል "እኛን የባንዳቹንና የአስካሪዎቹንም ልጆችና የልጅ-ልጆች ያካትታል"። አባቶቻችንን ለመውቀስ አፋችንን-ከማሾላችን በፊት "እኛስ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ምን አስተዋጽኦ አበርክተናል? ምንስ ልናበረክት እንችላለን?" የሚሉትን ከታሪክ-ሕሊና የማይጠፉ ጥያቄዎች ደጋግመን ልንጠይቅ ይገባናል።)

 

ወደዋናው ጉዳያችን እንመለስ፤ ወርሃ የካቲት ከማይዘነጋባቸውና ከሚታወስባቸው ነገሮች መካከል አንዱ በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም የተከሰቱት አስር መራራ የጽልመት ቀናት ናቸው። እነዚህም አስር ቀናት ከየካቲት 8 እስከ የካቲት 17/1929 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የሚመለከት ነው። በነዚህ ቀናት ውስጥ ለኢትዮጵያውያን የተደገሰው የሞት ድግስ እጅግ ዘግናኝና ኢ-ሰብአዊም ነበረ። መነሻዎቹ ሁለት ናቸው፤ የመጀመሪያው ለአርበኝነት ሙያ ወደደቡብ ዘምቶ የነበረውን የራስ ደስታ ጦር ለመምታት በርካታ ጦር አስከትሎ ሄዶ የነበረው ማርሻል ግራዚያኒ ሞቷል ተብሎ ወሬ ይናፈስበታል።

ይኼንንም ወሬ በስፋት ሲያስወሩበት የነበሩት እነአብራሃ ደቦጭና እነሞገስ አስገዶም እንደነበሩ ይገመታል (መቶ አለቃ መለሰልኝ አንለይ፤ በ1947 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፍ ላይ እንደገለጸው)። ሁለተኛውና ዋናው ዳፋ ደግሞ፤ "በየካቲት 12/1929 ዓ.ም በገነተ ልዑል ቤተ-መንግስት መግቢያ በር/በረንዳ ላይ በማርሻል ግራዚያኒ ላይ በነአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም አማካይነት የመግደል ሙከራ ስለተደረገበት ነው" ሲል ኢያን ካምፔል ያትታል (Ian Campbell; The Plot to Kill Graziani. 2003 ዓ.ም)።

 

በተጨማሪም፣ ግራዚያኒን በመግደሉ ሴራ ውስጥ "የንጉሠ ነገሥቱ ዋና ዋና ባለሟሎች እነደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ፣ እነጄነራል መኮንን ደነቀ፣ እና ሌሎችም በቀጥታ ከንጉሠ ነገሥቱ በተሰጣቸው መመሪያ መሠረት ወይም በተላከላቸው ደብዳቤ መሠረት ተካፍለዋል፤" ሲል ይገልፃል። ብርሃኑ ደቦጭ ለሙዚክ ሜይዴይ የመጽሐፍት ግምገማ ክበብ ተናጋሪዎች በየካቲት 2004 ዓ.ም እንደተናገረው፣ ይህንን ጥርጣሬ አምኖ ለመቀበል ይከብዳል። ምክንያቱም፣ የአብዛኞቹን ተጠርጣሪዎች ወይም ኢያን ካምፔል እንደሚለው "ሴረኞች" ቃል በቀጥታ ማግኘት ስላልቻለ ነው። ብዙዎቹ ለዚህ መጽሐፍ ዋቢ ተደርገው የተገለጹት የአርበኞች ማኅበር አባላትም ሆኑ የሴረኞቹ ልጆች ስለሴራው የቀጥታ ዕውቀትም ሆነ ተሳትፎ የሌላቸው በስማ በለው የሚናገሩ ሰዎች ናቸው። (በዚህ መጽሐፍ ላይ ሰፊ ውይይትና ክርክር ሊደረግበት እንደሚገባ እምነቴ የፀና ነው። ኢያን ካምፔል በዋነኝነት የመረጃ ምንጭ አድርጎ የተጠቀማቸውን ሰዎችና ሰነዶች እንደገና መመርመሩ የሚገባ ነው። ጉዳዩን ጉዳዬ ብሎ ስላጠናውና ስለለፋበት ምስጋና ይገባዋል።) 

 

መቶ አለቃም መለሰልኝም ሆነ ኢያን ካምፔል የፈለጉትን መነሻና መድረሻ ሊያቀርቡ ቢሞክሩ፣ ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 14 ቀን 1929 ዓ.ም የተፈጸመው ጭፍጨፋ በንጹኃን ላይ የተፈጸመ ግድያ ነው። ሰላማዊያኑ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ዕልቂት የተፈጁበት ይህ ዕለት የተፈጸማ በዕለተ ዐርብ 1929 ዓ.ም ነበር። ከዚህ ቀን ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ (ረቡዕ የካቲት 10/1929 ዓ.ም) ግራዚያኒ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ለሕዝቡም ሞተ ተብሎ የተወራው ስሕተት እንደነበረና ምንም ያለ መሆኑን ለማሳየት/ለማረጋገጥ ስለፈለገ በማግሥቱ የካቲት 11 ቀን 1929 ዓ.ም በዛሬው የየካቲት 12 አደባባይ ላይ እንዲሰበሰቡ አስለፈፈ። ሆኖም የተሰብሳቢው ቁጥር ስላነሰበትና ያሰበውን ያህል ትኩረት እንዳለገኘ ስለተሰማው፣ በማግሥቱ ዐርብ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ መልስ (ልክ ከጥዋቱ በ4፡00 ሰዓት ሕዝቡ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት እንዲሰበሰብ አዘዘ። ለነዲያንና ለችግረኞችም ብዙ ሊሬ እንደሚሰጥ ጭምር አስለፈፈ።

 

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ልክ በአራት ሰዓት ይጀመራል የተባለው ፕሮግራም ግብጻዊው አቡን፣ አቡነ ቄርሎስ ታምሜያለሁ ብሎ ስለቀረ/ስለዘገየ እስከሚመጣ ድረስ ለአንድ ሰዓት ያህል ዘገየ። ወታደር ተልኮ አበኑ ልክ 4፡55 ሰዓት ቤተ መንግሥት ደረሰ። ወንበር መጥቶለት ከግራዚያኒ በስተቀኝ በኩል ከከፍተኛ የፋሺስት ባለስልጣናት ጎን ተቀመጠ። ከግራዚያኒም በስተግራ በኩል ጄኔራል ጋሪባልዲ፣ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ (የአፄ ዮሐንስ የልጅ-ልጅ)፣ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት (የጎጃሙ ንጉስ ልጅ) ከሌሎች የኤርትራ ባንዶች ጋር ተጎልተው ነበር። ልክ 5፡00 ሲል ግራዚያኒ ሻኛው እንዳበጠ ኮርማ ቁና ቁና እየተነፈሰ ኢትዮጵያውያንን ያበሻቅጥ ጀመር። "ይኼው አለሁ!... መቷል እያላችሁ የምታወሩትና የምታስወሩት ሁሉ ከንቱ ሟርት ነው።" እያለ የኢትዮጵያን ሕዝብ በገዛ አገሩና በገዛ መሬቱ ላይ ያዋርደው ጀመር። (ግራዚያኒና ተባባሪዎቹ ቆመው የነበረው የቤተ መንግሥቱ በረንዳ ላይ ነበር።)

 

ልክ 5፡15 ሰዓት ገደማ ሲሆን አብራሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከበረንዳው በላይ ባለው ፎቅ ላይ/ግራዚያኒ ከቆመበት ሥፍራ ላይ ጥቁር ሸሚዝ ለብሰው፣ ኩታቸውን ተከናንበው ታዩ። ዓይኖቻቸው በንቃት ይንተገተጋሉ። ሰዓቱ ፍጥነቱን ጠብቆ ተጓዘ። ልክ 5፡30 ሲሆን ለነዲያን ምጽዋት መሥጠት ተጀመረ። በሥፍራው ከሦስት ሺህ ሁለት መቶ (3,200) በላይ ነዲያን ነበሩ። እንዲሁም ግብር ሊበሉ የመጡ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ግራዚያኒና ግብረ አበሮቹ ከቆሙበት ስፍራ በአሥር ወይም አሥራ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ ከበው ቆመው ነበር። ከሰዎቹም ፈንጠር ብለው ከዘጠና የማያንሱ መትረየሳቸውን የደገኑ ሶላቶዎችና አስካሪዎች በተጠንቀቅ ቆመዋል። ነዲያኑን ራቅ እንዲሉ ይገፋቸው ጀመር። ጫጫታና ውካታው ከፍ ብሎም ይሰማ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለአሥር ደቂቃዎች ያህል ትርምስምሱ የወጣ ትዕይንት ይታይ ጀመር።


ነገር ግን፣ በግምት ከ5፡40 እስከ 5፡45 ድረስ ባሉት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ተከታትለው ቦንቦች እነአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ካሉበት ደርብ ላይ ቁልቀል ተወረወሩ። የመጀመሪያው እንደተመረወረ ብዙዎቹ የመሰላቸው ለስብሰባው ማድመቂያ መድፍ የተተኮሰ ነበር። ሁለተኛው ሲወረወር ግን፣ አቡነ ቄርሎስና ግራዚያኒ መሬት ያዙ። በስተ ግራ በኩል ያሉትም ሁለት ጥበቃዎች ወዲያውኑ ሞቱ። ሦስተኛው ሲወረመርም፣ ግራዚያኒ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሊገባ ፊቱን አዙሮ መሸምጠጥ ጀምሮ ነበር። ሆኖም፣ የሦስተኛው ቦንብ ፍንጣሪዎች በርካታ ቦታ አቆሠሉት። ዳኒሎ ብቢሪንዴሊ የተባው የካሜራ ባለሙያም እየደማና እያቃሰተ የነበረውን ግራዚያኒን አንስቶ ከ5፡50 እስከ 6፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ መኪናው ከተተው። በፍጥነት ወደ ኦስፒዳሌ ኢታሊያኖ (የጣሊያን ሆስፒታል ለማለት ነው፤ የዛሬው "ራስ ደስታ ሆስፒታል" መሆኑን ልብ ይሏል፤) ወሰዱት።

ከየካቲት 12 ቀን 1929ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓትም ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 1929 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በግፍ ተፈጁ። ብዙ ጊዜ የሚነገረው ቁጥር በአዲስ አበባ ብቻ የተፈፀመውን ግድያ የሚያሳይ ነው። በፋሺስቱ ግራዚያኒና በግበረ አበሮቹ በኢትዮጵያዊያኑም ትብብር አመላው ኢትዮጵያ አውራጃችና ቀበሌዎች ባልቴት፣ ሽማግሌ፣ ሕፃን፣ ወጣት፣ ካሕን፣ ሴት፣ እስላም፣ ክርስቲያን፣ አረማዊ፣ ማንም ከማንም ሳይለይ ተፈጀ። ፕ/ር መስፍን "አገቱኒ፣ ተምረን ወጣን" ባሉት መጽሐፋቸው እንደገለጹት የአምስት አመት ልጅ ሳይቀር አልጋ ስር ተደብቆ ነበር ያንን የጽልመት ቀን ለጥቂት የተረፈው።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩትና በወቅቱ በስፍራው የነበሩት አሃዱ ሳቡሬ በየካቲት 12 ቀን 1947 ዓ.ም እንደገለጹት፣ "ኢትዮጵያን መሬቷን እንጂ ሕዝቧን አንፈልግም በሚል ዘረኛነት" የፈጀውና ያስፈጀው ግራዚያኒ፣ በከተማ ነዋሪ የነበሩትን ኢትዮጵያውያን እርጉዝና ሽባዎችን ሳይቀር ነበር ያስፈጃቸው። ግድያው በመትረየስና በጠብ ምንጃ ብቻ አልነበረም። በአካፋ ተጨፍጭፈው፣ በዶማም ተፈልጠው፣ በፋስና በመጥረቢያም ተቆራርጠው የሞቱትን ቤቱ ይቁጠራቸው። ከቤታቸው ለመውጣትና ለማምለጥ ያልቻሉትን ባልቴቶችና ሽማግላችም ቤቱን የኋሊት እየዘጉባቸው ነበር እሳት ጎጇቸው ላይ የለኮሱባቸው። ልብ ማለት ያለብን ቁም ነገር አለ፤ ፋሺሽት ብቻውን አይፈደለም ይኼንን ግፍ የፈጸመው። የኛው ሰዎች ተባባሪ (ባንዳና አስቃሪ) ሆነው ነው እልቂቱን ያባባሱት።

በዚህ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት ሢፈጸም በነበረው ግፍ ወቅት፣ የኢትዮጵያውያኑ ሰማዕታት አስክሬን በገዛ አገሩ ጥርኝ አፈር ተነፍጎ በየጎዳናው ተዘርሮ፣ ደሙም እንደሐምሌ ጎርፍ ሲጥለቀለቅ፣ በገዛ ቤታቸው የተቃጠሉትና የቤቱ ቃጠሎ ነበልባል ደግሞ ጢስ እስከ ሰማይ ሲያርግ ያዩ የዐይን ምስክሮች ዛሬም አሉ። በዚያን ጊዜ፣ የኢትዮጵያውያኑ ዕንባ እስከ ሰማየ-ሰማያት ደርሶ "እስከ ማዕዜኑ ትረስአኒ ለግሙራ" እያለ ሲጮህ ይሰማ ነበር። በአራተኛው ቀን (የካቲት 15/1929 ዓ.ም) ግን ነገሮች ጋብ ያሉ መሰሉ። የግራዚያኒም ቁጣ የበረደ መሰለ። ለከተማዎቹም ጽዳት ሲባል የሰማዕታቱ አስክሬን አፈር እንዲቀምስ ተደረገ። ብዙዎቹ በቡልዶዘር አማካይነት በጅምላ ተቀበሩ። እነዚህ የጅምላ መቃብሮች (ብዙዎቹ) ዛሬም በቅጡ አይታወቁም። የተወሰኑት ግን ለአጽማቸው ማረፊያና መታሰቢያ ተብሎ በቅድስት ሥላሴ ሃውልት ቆሞላቸዋል።

የዚህ ግፍና ፋሺስታዊ ስራ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበረው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሃውልት ቆሞለት፣ መናፈሻም ተሰርቶለታል። በቅርቡ ደግሞ፣ ቤርሎስኮኒ የሚባለው የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ሞሶሎኒን የሚያመሰግን ቃል ሲናገር ተደምጧል። ጣሊያን ተመልሳ ወደ ኢትዮጵያውያንና ወደ አፍሪካውያን ጠላቶች አስተሳሰብ እየገባች ነው። ክብር ለማይገባቸው ግፈኞች፣ ክብርንና ሞገስን የሚሰጡትን ሁሉ በያለንበት ሆነን ልንቃወማቸው ይገባል። (ክብር ለማይገባቸው ክብርን የሚሰጡ ክብረ-ቢሶች ብቻ ናቸው።) ዛሬውኑ ፋሺዝምን ማንሰራራት በሚደግፈው የኢጣሊያን መንግሥትና አንዳንድ ደናቁርት ላይ እንረባረብ። የኢጣሊያን ኤምባሲዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ተሰባስበን ድምጻችንን እናሰማ። በማኅበራዊ ድረ-ገፆችም ላይ ተቃውሟችንን እናሰማ። በተጨማሪም፣ የተለያዩ የግፍ ድርጊቶቻቸውን በመጽሐፍም ሆነ በፊልም አቀናብረን ለእውነቱ ከሰማዕታቱ ጋር እንቁም። በግፍ ለፈሰሰው ሰላማዊ ኢትዮጵያውያን ደም የተከፈለው 30 ሚሊዮን ዶላር በቂ አይደለምና የጦር ካሳ ኢጣሊያ እንድትከፍል የተደራጀ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ እንቀላቀል። አጠገባችን ያለውን ለኢትዮጵያውያን ክብርና ሞገስ የማይቆም ግድግዳ በጋራ እናስወግድ። (የሳምንት ሰዎች ይበለን!)


በሳምናታዊው የአዲስጉዳይ መጽሔት ቅጽ 7፣ ቁ. 152 ላይ፤ በየካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣ ነው።

ሰሎሞን ተሰማ ጂ.
http://semnaworeq.blogspot.se/  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ