የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አድራሾች አልታወቁም
በሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ የግድያ ሙከራው የተቃጣበት ስፍራ
ዶ/ር ዐቢይ የግድያ ሙከራውን አውግዘዋል
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 9, 2020)፦ ዛሬ ጠዋት ወደ ቢሯቸው ሲያቀኑ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቀ ጥቃት አድራሾች የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ደኅንነቱ በተጠበቀ ስፍራ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ወደ ቢሮ በሚያቀኑበት ወቅት በተቃጣው የግድያ ሙከራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ዐይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከግድያ ሙከራው በኋላም ሚኒስትር አብደላ በትዊተር ገጻቸው በመልካም ሁኔታ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም የግድያ ሙከራውን በተመለከተ ባሰፈሩት ተጨማሪ መልእክት፤ “ምንም ነገር ቢፈጠር ለውጡን የሚያቆመው ነገር የለም” የሚል ነው። የግድያ ሙከራውን ያደረጉት ወገኖች ጥቃቱ ሊፈጽሙ የሞከሩት በፈንጂና በጥይት እንደኾነ የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ የኾኑት ፋይሳል ሳሌህ ለመገናኛ በዙኀን ገልጸዋል።
ይህንን የግድያ ሙከራ በማውገዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራውን፤ “በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ ዛሬ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አወግዛላሁ” በማለት ገልጸዋል።
የሱዳን ሕዝብ ሰላሙን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ የሚደነቅ እርምጃ ስለመውሰዱ ያስታወሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ በዕለቱ እንደተፈጸመው ዐይነት ክስተቶ የሱዳንን መረጋጋትና የለውጥ ጉዞ ሊያደናቅፍ እንደማይገባም የግድያ ሙከራውን አስመልክቶ ባሰፈሩት መልእት ገልጸዋል። (ኢዛ)



