የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለ15 ቀን እንዲዘጉ ተወሰነ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ ሲባል መኾኑ ተገልጿል
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 18, 2020)፦ በየዕለቱ በአማካይ 18 ሺህ የሚገመቱ ተገልጋዮችን ያስተናግዳሉ የተባሉ ሦስት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሲባል ለ15 ቀናት እንደሚዘጉ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አስታወቁ።
ወረርሽኙን ለመከላከል ወይም አደጋውን ለመቀነስ እንዲቻል ከፍርድ ቤቱ ልዩ ሁኔታ በመነሳት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራር የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን፤ ዛሬ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የጠቅላይ ፍርድ ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ሥርጭትን መከላከል በተመለከተ የተሠጠ መግለጫ
ቀን፡- መጋቢት 9/ 2012 ዓ.ም.
ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ መኾኑን በዓለም ጤና ድርጅት የታወጀ ሲሆን፤ እስከ ዛሬ ድረስ ይህ ቫይረስ በአገራችን በስድስት ሰዎች ላይ የታየ መኾኑን መንግሥት አሳውቋል፡፡ ይህ ወረርሽን የሚተላለፈው በአብዛኛው በሰዎች መካከል በሚኖር ንክኪ እና የተጠጋጋ ግንኙነት መኾኑ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ በመኾኑ ከፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ባሕሪ አንጻር ወረርሽኙ በፍርድ ቤቱ ማኅበረሰብ እና በፍርድ ቤት ተገልጋዮች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በየዕለቱ ወደ ፌደራል ፍርድ ቤት የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥር በአማካይ ሲታይ በሶስቱ ፍርድ ቤቶች ከ18000 በላይ ሊገመት ይችላል፡፡ ይህ በርካታ ከሳሽ/ ተከሳሻ ወይም በርካታ ምስክሮች ያሉባቸውን መዝገቦች ሳይጨምር ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ወይም አደጋውን ለመቀነስ እንዲያስችል ከፍርድ ቤቱ ልዩ ሁኔታ በመነሳት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራር የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዚሁ መሰረት፡-
1. ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10-24 ድረስ ለ15 ቀናት በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ እና በእነዚህ ግዜያቶች ተቀጥረው የነበሩ መዛግብት ከመጋቢት 24 በኋላ ባሉት ቀናቶች እንደየጉዳዮቹ ዓይነት ዳኞች ከረዳት ዳኞች ጋር በመሆን ቀጠሮ ያሸጋሽጋሉ፤
2. ዳኞች የሚሰጧቸው ተለዋጭ ቀጠሮዎች ተከራካሪ ወገኖች እንዲያውቁት ለማድረግ በኤስ ኤም ኤስ መልእክት እንዲሁም በፍርድ ቤት ግቢዎች የመዝገቦች ዝርዝር እና የቀጠሮ ቀኞች እንዲለጠፉ ይደረጋል፤
3. በአጋጠመው አስገዳጅ ሁኔታ ቀጠሮ በመተላለፉ ምክንያት ወደ ፊት ሊያጋጥም የሚችለውን ክምችት ለመቀነስ ዳኞች ትኩረት አድረገው በሙሉ አቅማቸው ለውሳኔ የደረሱ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ፤
4. ፍርድ ቤቶች የጊዜ ቀጠሮ፤ የዋስትና እና ሌሎች መሰል እጅግ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ ለምሳሌ ከአገር ጸጥታና ደኅንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች እየመዘኑ ያስተናግዳሉ፤
5. ከመጋቢት 10-24 የይርጋ ጊዜቸው ሊያልፉባቸው ከሚችሉ መዝገቦች ውጪ ያሉ አዳዲስ ክሶች አይከፈቱም፤
6. ከመጋቢት 10-24 ባሉት ግዜያቶች ከክልል የሚመጡ ባለጉዳዮች ዛሬ በተሰጠው ውሳኔ ምክንያት የይግባኝ ጊዜያቸው የሚያልፉ ጉዳዮች የይግባኝ ማስፈቀጃ ጥያቄዎች በሚስተናገዱበት ጊዜ ከግምት የሚገባ ይሆናል፡፡
7. ከክልል የሚመጡ ባለጉዳዮች እንዳይጉላሉ የክልል ፍርድ ቤቶች የተፈረደባቸው ተከራካሪዎች በአፈጻጸም መገደዳደቸው እንዲቆይ እንዲያደርጉ ለክልል ፍርድ ቤቶች መልእክት ይተላለፋል፡፡
8. የፌደራል ፍ/ቤቱ በከፊል እንዲዘጋ የተወሰነበት ምክንያት ወደ ፍርድ ቤቱ የሚመጡ ተገልጋዮች ፍሰት ለመግታት ነው፡፡ ስለዚህ በሚቀጥሉት 15 ቀናት በልዩ ሁኔታ ወደ ፍርድ ቤታችን የሚመጡ ባለጉዳዮች በተቻለ መጠን ለብቻቸው እንዲመጡና ማህበራዊ ቅርርቦችን እንዲቀንሱ እንጠይቃለን፡፡
9. የፍርድ ቤቱ የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በተመለከተ ነፍሰጡር ሴቶች፣ የታወቀ ሕመም ያለባቸው ሠራተኞች እረፍት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
10. በዚህ አጋጣሚ የ COVID 19 ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት እና የክትትል እርምጃዎች እናደንቃለን፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቱ ይህንን ዓለምዓቀፋዊ የጤና አደጋ በወገኖቻችን ጤና፣ ማህበራዊ ሕይወትና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳያስከትል በቅርብ በመከታተል አስፈላጊ እርምጃዎችን የሚወሰድ መኾኑን እንገልጻለን፡፡
የፍርድ ቤቱ አመራሮች፣ ዳኞች፣ ሠራተኞች እና የፍርድ ቤት ማኅበረሰብ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከዚህ በላይ የተቀመጡት ውሳኔዎች ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ተባብረን መስራት የሚጠበቅብን መኾኑን እየገለጽን ወደ ፊት የሚከሰቱ ሁኔታዎች እየተከታተልን ወቅታዊ መረጃ እንደምንሰጥ እናሳውቃለን።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት



