የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሕዝብ ጤንነትና ደኅንነት ላይ ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዘ

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም የሚወሰደውን እርምጃ አስታውቋል
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 29, 2020)፦ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በዚህ ወሳኝ ወቅት በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ መታዘዙን አስታወቀ።
ከጽሕፈት ቤቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በወጣው መግለጫ የሕብረተሰብ ጤና መረጃን ማዛባትና በዜጎች መካከል ፍርሃትና ረብሻን መንዛት በወንጀል የሚያስጠይቅ አገራዊ አንድነትን የማናጋት ተግባር ነው ብሎ፤ በኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ላይ መረጃ የሚሠጡት አካላት ጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መኾናቸውን ገልጿል።
ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ወረርሽኙን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሠራጩ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና፤ ይህንን ባያደርጉ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድና በዚህ ረገድ በሕግ ተፈፃሚ የሚያደርጋቸውን ሕግጋትም አስታውቆ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያወጡዋቸው መግለጫዎች የሚከተሉት ናቸው። (ኢዛ)
ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መግለጫ
የጤና ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰት፣ የተሳሳተ መረጃን ተቀብሎ ማሠራጨት ከቀውሱ እኩል ጎጂ ነው። ማንኛውም ሰው እንዲህ ባለ ጊዜ የሐሰት ዜናዎችን ለማስቆም የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት።
የፌደራል መንግሥት #ኮቪድ19ን በተመለከተ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት፣ መረጃን የማደራጀት እና በየዕለቱ የማሠራጨት ሥራን እያከናወነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣው ኮሚቴ እና ሌሎች ዐበይት ኮሚቴዎች ያላቸውን ወቅታዊ የሥራ ክንውን እያስተባበረ እና መረጃን እያስተላለፈ መኾኑ ይታወቃል።
ሕዝቡ እንዲህ ባለው አስከፊ ጊዜ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚንቀሳቀሱ አካላት ነቅቶ ራሱን እንዲጠብቅ ይጠየቃል። የሕብረተሰብ ጤና መረጃን ማዛባት እና በዜጎች መካከል ፍርሃት እና ረብሻን መንዛት በወንጀል የሚያስጠይቅ አገራዊ አንድነትን የማናጋት ተግባር ነው። በ#ኮቪድ19 ላይ መረጃን የሚሠጡ ዐበይት አካላት የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ናቸው።
በዚህ ፈታኝ ወቅት በሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሽብር የሚነዙ አካላት ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት ሕግ የማስከበር ተግባራቸውን በጥብቅ እንዲያከናውኑ የታዘዙ መኾኑንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይገልጣል።
ትናንት ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተሠጠው መግለጫ
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለ፣ በአህጉራችን አፍሪካ፣ እንዲሁም በአገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ሥጋት የደቀነ ወረርሽኝ ነው። በአሁኑ ወቅት ይህን ወረርሽኝ መግታት እና መከላከል ትልቅ አገራዊ የትኩረት አጀንዳ ነው። የዜጎችን ሕይወት እና ጤና፤ የአገርን ሕልውና እና ደኅንነት አደጋ ላይ የጣለውን የዚህን ወረርሽኝ ሥርጭት ለመመከት የሁላችንም ጥረት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው። እስካሁን በተለያዩ አገራት የተከሰተውን የወረርሽኙን ሥርጭት፣ እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት እና የአገራችን የጤና ባለሙያዎች እና ተቋማት የሚያቀርቡዋቸውን ሙያዊ መረጃዎች እና ምክሮች ከግምት በማስገባት፤ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል። ሕዝቡ ስለበሽታው መረጃ ኖሮት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዲችል ስለወረርሽኙ ባሕርያት እና መተላለፊያ መንገዶች በየጊዜው ከሚሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ የኾኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች በየደረጃው እንዲወሰዱ መንግሥት ውሳኔ ማስተላለፉ እና መመሪያዎች መሥጠታቸው ይታወሳል።
እነዚህን ውሳኔዎች እና መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እስካሁን ያለው ሁኔታ በቂ እና አስተማማኝ ነው ለማለት አይቻልም። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ አስፈላጊው መረጃ ለሕዝቡ እንዲደርስ የሚደረገው ጥረት ተጥናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ነገር ግን ኾን ብለው እና ለሕዝብ ደኅንነት እጅግ አደገኛ በኾነ መልኩ አግባብነት ባላቸው የመንግሥት መዋቅሮች የሚሠጡ መመሪያዎችን እየጣሱ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም ኾን ብለው ወረርሽኙን በተመለከተ አደገኛ የሐሰተኛ መረጃ በማሠራጨት ሕዝብን በሚያሸብሩ፣ እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ አላግባብ የኾነ ትርፍ ለማካበት የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ከሕገ-ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።
የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2002 ስለተላላፊ በሽታዎች ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፤ ይህ አዋጅ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፤ “ማንኛውም ወደ አገር የሚገባ ወይም ከአገር የሚወጣ መንገደኛ አገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ መስፈርቶች መሠረት … በተላላፊ በሽታ ሲጠረጠር ለምርመራ የመተባበር ግዴታ አለበት”። እንዲሁም “… ወረርሽኝ ካለበት ቦታ የመጣ ሰው ወደ አገር አንዳይገባ ሊታገድ ይችላል”፡፡ ይሄው አዋጅ በተጨማሪም “አግባብ ያለው የጤና ባለሙያ በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተያዘን ወይም የተጠረጠረን ማንኛውም ሰው ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ’’ ማድረግ እንዳለበት፤ በተጨማሪም “በወረርሽኝ ተላላፊ በሽታ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ለምርመራ፣ ለሕክምና … ፈቃደኛ መኾን” እንዳለበት ተደንግጎዋል። በአዋጁ መሠረት እነዚህን ድንጋጌዎች መጣስ እስከ ስድስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ፤ በአንቀጽ 514 ኾን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ተላላፊ በሽታን ማስተላለፍን በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጎ ደንግጎዋል። ይህን አንቀጽ በመጣስ የሚፈጸም ወንጀል እስከ አሥር ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ሲሆን፤ በተለይም ተላላፊው በሽታ በወረርሽኝ ወይም በኢፒደሚክ መልክ የተከሰተ ሲሆን፣ እንደነገሩ ክብደት ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ ያሳያል። በተጨማሪም የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 830 የሕዝብ ጤና እና ጤናማነትን ለመቆጣጠር በሚል ርዕስ ባሉት ደንጋጌዎች እንደተገለጸው፣ በሽታዎችን በተለይም ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኝ ስለመከላከል፣ መኖራቸውን ስለማሳወቅ፣ ለመከላከል የሚረዱ ሕክምናዎችን ስለማድረግ ወይም ስለመቆጣጠር የወጣን መመሪያ መጣስ እሰከ ሦስት ወር በሚደርስ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል ነው።
በተጨማሪም ለሕዝብ ጤና አስጊ የኾነ አደጋ እንደሚደርስ በማስፈራራት ኾን ብሎ ሕዝብን ያሸበረ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ክብደት ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 485 ተደንግጎዋል።
የኮርኖ ቫይረስ ሥርጭትን አስመልክቶ የሚሠጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ጥቅሙ በቅድሚያ ለራስ፣ ቀጥሎም በዙሪያችን ላሉ ቤተሰቦቻችን፣ ወገኖችን እና ብሎም ለአገር ነው። ይህን በመገንዘብ፣ ሁላችንም ተገቢውን ጥንቃቄ አቅም በፈቀደ መጠን እንድናደርግ ጥሪያችንን እያቀረብን፤ ነገር ግን ጉልህ በኾነ መልኩ የቅደመ ጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጣስ የሕዝብን ጤንነት እና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥሉ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ፤ እንዲሁም የኮሮና ቫይርስ ሥጋትን ሰበብ አድርገው ኾን ብሎ ሕዝብ የማሸበር ወንጀል በሚፈጽሙ ላይ፣ ከላይ በተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎችና ሌሎች አጋባብነት ያላቸውን ሕጎች መሠረት በማድረግ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ በአፋጣኝ ለመውሰድ የምንገደድ መኾኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ