በ24 ሰዓት ምርመራ ዘጠኝ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኙ
የጤና ሚኒስቴር
በአንድ ቀን ከፍተኛ ተጠቂ መገኘቱ ሪፖርት የተደረገበት ቀን ኾኗል
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 10, 2020)፦ በኢትዮጵያ በ24 ሰዓት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቫይረሱ ተጠቂ የተገኘበትና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 65 መድረሱ ተመለከተ። የጤና ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በተደረገ ምርመራ አዲስ ዘጠኝ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ሪፖርት ባደረገው መረጃ፤ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ዘጠኝ ተጠቂዎች የተገኙበት ሲሆን፣ ይህም እስካሁን በየዕለቱ ሪፖርት ከተደረጉት ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ኾኗል።
ዘጠኙ አዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙት 442 በሚኾኑት ላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ነው። ከዘጠኙ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ ሰባቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የሕንድና የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ናቸው።
ከዕለታዊው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፤ ዘጠኙም የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆን፤ ሁሉም በለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው። (ኢዛ)



