በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ያገገሙት 50 ደርሰዋል
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
በዛሬው ሪፖርት 933 ሰዎች ተመርምረው፤ አንድ በቫይረሱ የተጠቃ ተገኝቷል
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 27, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ሪፖርት ከተደረጉትና በለይቶ ሕክምና መስጫ ማዕከል ከሚገኙት ታማሚዎች ውስጥ ማገገም የቻሉት 50 ደርሰዋል። አንድ ሰው በቫይረሱ የተጠቃ ተገኝቷል።
ዛሬ ሚያዝያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 933 ሰዎች ተመርምረው፤ የላቦራቶሪ ውጤቱ አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙ በመረጋገጡ፤ እስካሁን የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 124 አድርሶታል።
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ይልቅ እያገገሙ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ትናንት 12 አዳዲስ ያገገሙ ሰዎች በመገኘታቸው፤ ያገገሙት ሰዎችን ቁጥር 41 አድርሶት የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ዘጠኝ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች በመታከላቸው፤ ከበሽታው ያገገሙት ቁጥር 50 ሊደርስ ችሏል።
በአሁኑ ወቅት በሕክምና ላይ የሚገኙት የበሽታው ተጠቂዎች 69 ሊደርስ መቻሉን ከጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመላክቷል። (ኢዛ)



