በ24 ሰዓት ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች የኮሮና ምርመራ ተደረገላቸው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
ከፍተኛ ምርመራ ቁጥር በተደረገበት ዕለት አንድም ተጠቂ አልተገኘም
የተመርማሪዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ ደርሷል
ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 2, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተነገረበት ጊዜ ወዲህ እና በኢትዮጵያ የኮሮና የላቦራቶሪ ምርመራ ከተጀመረ ጀምሮ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራ የተካሔደ ቢኾንም፤ አንድም ተጠቂ አለመገኘቱ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን ይፋ ባደረገው ዕለታዊ መረጃ፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 2016 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ቢኾንም፤ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልተገኘም። በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሠረት፤ በትናንትናው ዕለት 18754 የነበሩት ጠቅላላ የተመርማሪዎች ቁጥር 20,770 ሊደርስ ችሏል።
በዛሬው መረጃ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች በማገገማቸው አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 69 ደርሷል። በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ማቆያ ሕክምና እየተደረገላቸው ያሉት ደግሞ 59 ናቸው። (ኢዛ)



