የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር 145 ደርሷል፤ ሞት በአንድ ጨመረ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
የ75 ዓመት ወይዘሮ በቫይረሱ ሞተዋል፤ ያገገሙ በ16 ጨምሮ 91 ደርሷል
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 5, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 145 ከፍ ያለ ሲሆን፤ በቫይረሱ መጠቃታቸው የታወቀ የ75 ዓመት ወይዘሮ ሕይወታቸው በማለፉ በዚህ ወረርሽኝ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አራት መድረሱ ታውቋል።
ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጤና ሚኒስቴር በወጣው መረጃ መሠረት፤ በ24 ሰዓት ውስጥ 1,047 የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ፤ አምስት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በመረጋገጡ፤ የተጠቂዎች ቁጥር ትናንት ከነበረው በአምስት ጨምሮ 145 ሊደርስ ችሏል።
በመረጃው መሠረት ከአምስቱ አዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች አንድዋ የኾኑት የ75 ዓመት ወይዘሮ ሕይወታቸው አልፏል።
ወይዘሮዋ በተጓዳኝ ሕመም ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ ሲሆን፤ በገጠማቸው የመተንፈስ ችግር ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ናሙና ከተወሰደ በኋላ በተደረገ ምርመራ፤ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከመረጋገጡ በፊት ሕይወታቸው ያለፈ መኾኑ ተገልጿል።
ቀሪዎቹ አራቱ ግለሰቦች ደግሞ የስምንት፣ የ25፣ የ22 እና የ19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው መኾናቸው ታውቋል። ሁለቱ ከጅቡቲ ተመልሰው በአፋር አስገድዶ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ የ25 እና የ22 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወንዶች ናቸው።
የስምንትና የ19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ደግሞ የውጭ ጉዞ የሌላቸው፤ ግን በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው ሴቶች ናቸው።
ዛሬ ከተገለጸው የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱና አራት (ከሟች ጋር አምስት) አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው በተጨማሪ፤ 16 አዲስ ያገገሙ ሰዎች ተገኝተዋል። ይህም በአጠቃላይ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር 91 ሊደርስ ችሏል። በሕክምና ላይ የሚገኙት ደግሞ ወደ 48 ዝቅ ያለ መኾኑ ታውቋል።
ሟቿን ወይዘሮ ጨምሮ አምስቱ አዳዲስ ከቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ፤ ሁለቱ በአፋር፣ ሁለቱ በአዲስ አበባ (ሟቿና የስምንት ዓመቷ ሕጻን)፣ እንዲሁም የ19 ዓመቷ በኦሮሚያ የተገኙ ናቸው። (ኢዛ)



