በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ረቡዕ ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.)
በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በሁለት ሳምንት 300 በመቶ ጨምሯል
እስካሁን በቫይረሱ ከተጠቁት 65 የጤና ባለሙያዎች ናቸው
ጤና ጥበቃ የወረርሽኙ ስፋት አስጊ መኾኑን ገልጿል
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 3, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መያዛቸው እየጨመረ ከመምጣቱም ባሻገር፤ በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው የሚያልፉ ሰዎች በተከታታይ እየተገለጸ መምጣቱ፤ ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ እያደረገው ነው።
በዛሬው (ረቡዕ ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.) የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ ተጨማሪ የሦስት ሰዎች ሕይወት ያለፈ በመኾኑ፤ የሟቾች ቁጥር 17 ደርሷል። በሁለት ወር ከሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው ከሞቱት ሰዎች ውስጥ ከ10 በላይ የሚኾኑት ሕይወታቸው ያለፈው በዚህ አንድ ሳምንት ውስጥ ነው።
በመኾኑም በየዕለቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከመጨመር ባሻገር፤ በቫይረሱ ተጠቅተው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፤ ወረርሽኙ ስር እየሰደደ አደገኛም እየኾነ መምጣቱን አመልክቷል። በአሁኑ ወቅትም በጽኑ ሕመም ላይ ያሉ ስድስት ሰዎች አሉ።
ከዕለታዊው የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፤ ዛሬ ከተመዘገበው ሦስት ሞት ሌላ ለ4,120 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ 142 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ይህም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ መጠቃታቸው የታወቁ ሰዎችን ቁጥር 1,486 አድርሶታል።
ከ142ቱ አዲስ ተጠቂዎች ውስጥ አሁንም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በእጅጉ ብልጫ መያዛቸውን አሳይቷል። 126ቱ የተገኙት ከአዲስ አበባ በመኾኑም ከተማው ወረርሽኙ አይሎ የሚታይባት መኾኗን አረጋግጧል።
በዛሬው መረጃ መሠረት ከአፋር ክልል ሁለት፣ ከኦሮሚያ ክልል ሰባት፣ ከአማራ ክልል ስድስት፣ እንዲሁም አንድ ከሶማሌ ክልል የተገኙ ናቸው።
የአገሪቱን ወቅታዊ የወረርሽኙን ሥርጭት በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር ጨምሮ እንደገለጸው ደግሞ፤ የቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መኾኑን ነው።
ለዚህም ማሳያ የሚኾነው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ከተገለጸ ጊዜ ጀምሮ፤ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ300 በመቶ በላይ ጨምሯል በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት አመልክቷል።
በአንፃሩ 15 ያገገሙ ሰዎች በመገኘታቸው አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 246 ደርሷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 65ቱ የጤና ባለሙያዎች መኾናቸው ታውቋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ እንደገለጹት 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና እነዚህም የጤና ባለሙያዎች በአብዛኛው በአዲስ አበባ በሚገኙ የጤና ተቋማት እየሠሩ የነበሩ ናቸው። (ኢዛ)



