የኦሮሚያ ፖሊስ በግድያና በዘረፋ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን 48 ሰዎች በቁጥጥር ስር አዋለ
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ግርማ ገላን
ግለሰቦቹ አባ ቶርቤ በሚል ስያሜ የተደራጁ ናቸው
ኦነግ ሸኔ በቀለምት ወለጋ 114 ሰዎች ገድሏል
ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የሕወሓት ስም ተጠቅሷል
ኢዛ (ዓርብ ግንቦት ፳፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 5, 2020)፦ በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች በግድያና በዘረፋ ወንጀል ላይ የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና እነዚህ ግለሰኦች “አባ ቶርቤ” በሚል ስያሜ የተደራጁ ስለመኾናቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ግርማ ገላን በሰጡት መግለጫ በቄሌም ወለጋ ዞን፣ በነቀምቴና በቡራዩ ከተሞች ሲፈጸሙ በነበሩ ጥፋቶች ላይ ትእዛዝ ሲሰጡ የነበሩ ኃይሎችንና ጥፋት የፈጸሙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልጸዋል።
በኦነግ ሸኔ የሚመራውና “አባ ቶርቤ” በሚል ስያሜ ተደራጅተው የሰዎችን ሕይወት ሲያጠፉ የነበሩት እነዚህ ግለሰቦች የተያዙት፤ በተደረገ ፍተሻና ክትትል መኾኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ሙሉ መረጃ አለው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አራት የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ወንጀሎች ሲፈጽሙ ነበር።
እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ኃላፊዎችንና ባለሀብቶችን ሕይወት በመጥፋት፣ በአክቲቪስት ስም የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ሕዝብ ውስጥ ውዥንብር በመፍጠር ጭምር ሲሠሩ ነበርም ተብሏል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በኦነግ ሸኔ ስም በምዕራብ ቄሌም ወለጋ ውስጥ 212 ሰዎች ላይ ጉዳይ መድረሱንና በተለያዩ ከተሞች በኦነግ ሸኔ 114 ሰዎች መገደላቸውንም ዘገባው ያሳያል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መረዳት እንደሚቻለውም፤ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ሥልጠና ጭምር የወሰዱ ስለመኾኑ ማረጋገጥ ስለመቻሉ ተጠቅሷል። (ኢዛ)



