ኬሪያ ኢብራሒም

ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም

ያሉት መቀሌ ነው፤ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አላስገቡም

ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 8, 2020)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታወቁ።

ዛሬ ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ለድምፂ ወያኔ ቴሌቭዝን በሰጡት መግለጫ፤ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቃቸው አንዱ ምክንያት፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ትርጉምን ባለመቀበል ጭምር ነው።

“አምባገነናዊ መንግሥት ወደመመሥረት ደርሰናል” ያሉት ወ/ሮ ኬሪያ፤ ምክር ቤቱ ባለው አምባገነናዊ አካሔድ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ውሳኔ እንዲተላለፍ እየተደረገ ነው በማለት ወቅሰዋል።

ወይዘሮ ኬሪያ ይህንን ውሳኔያቸውን በድምፂ ወያኔ በሰጡት መግለጫ ነው ያስታወቁት። በሌላ በኩል ግን ከሕገ መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በግልጽ እያሳወቁ ስለነበር፤ ከኃላፊነታቸው ይለቃሉ የሚለው አመለካከት ጎልቶ ይታይ ነበር።

ወይዘሮ ኬሪያ ይህንን መግለጫ የሰጡት ከመቀሌ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ወይዘሮዋ ከሥራ መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አለማስገባታቸውን ጠቁመዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አፈ ጉባዔዋ ኃላፊነት መልቀቅ ደግሞ፤ በእርሳቸው ምትክ ምክትላቸው አቶ መሐመድ ረሽድ ሐጂ ይተኳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ወይዘሮ ኬሪያ የሕወሓት አባል ሲኾኑ በቀድሞው አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ምትክ ከሚያዝያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴሬሽኑ አፈ ጉባዔ ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ