CPJ, Committee to Protect JournalistsEthiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፳፬-24 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 4, 2008)፦ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲ.ፒ.ጄ. እንዳስታወቀው፣ በዘንድሮው የፈረንጆች (2008) ዓመት 29 ጋዜጠኞች በሥራቸው ላይ እያሉ ተገድለዋል።

 

ሲ.ፒ.ጄ. እንዳለው፣ ጋዜጠኞቹ የተገደሉት በዘገባቸው የተነሳ ሆን ተብሎ፣ አልያም ከሚሠሩለት ተቋም ጋር በተያያዘ ነው።

 

በዓመቱ የመጀመሪያው የሞት ሰለባ የሆነው የ38 ዓመቱ የኖርዌይ “ትስሎ ዴይሊ ዳግብላዴት” ጋዜጠኛ የሆነው ካርስታን ቶማስን ሲሆን፣ የተገደለውም በአፍጋኒስታን ካቡል የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በገባ በ15ኛው ቀን ነበር።

 

በተለያዩ አካባቢዎች ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል አንድ በቦሊቪያ፣ አንድ በካምቦዲያ፣ ሦስት በጆርጂያ፣ አንድ በሕንድ፣ 10 በኢራቅ፣ አንድ እስራኤል በምታስተዳድራቸው ግዛቶች፣ ሦስት በፓኪስታን፣ ሁለት በፊሊፒንስ፣ ሁለት በሩስያ፣ ሁለት በሶማሊያ፣ አንድ በሲሪላንካ እና አንድ በታይላንድ ይገኙበታል።

 

በሶማሊያ ከተገደሉት ሁለት ጋዜጠኞች መካከል ለሶማሊያ ብሔራዊ የዜና አገልግሎት ያገለግል የነበረው የ38 ዓመቱ ሐሰን ካፊ ሃሬድ የሚገኝበት ሲሆን፣ የተገደለውም በደቡብ ምዕራቧ የወደብ ከተማ የሕክምና ዕርዳታ በሚሰጥ ተሽከርካሪ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት መሆኑ ታውቋል።

 

ናስቴህ ዳሂር የተባለው ሌላው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ፣ የሶማሊያ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ሕብረት ም/ል ሊቀመንበር ሲሆን፣ የተገደለው ከኢንተርኔት ካፌ ወጥቶ ወደ ቤቱ በእግሩ ሲጓዝ በሁለት ታጣቂዎች ነበር። 15 ያህል ጋዜጠኞች ደግሞ በማን እንደተገደሉ አለመታወቁን ሲ.ፒ.ጄ. ገልጿል።

 

ከእነዚህ ጋዜጠኞች ውስጥ አንዳንዶቹ በጥይት ተደብድበው፣ አንዳንዶቹም በግርፋት ተሰቃይተው፣ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ከቀያቸው ርቀው ተገድለው መጣላቸውን ሲ.ፒ.ጄ. ፖሊስን ዋቢ አድርጎ አስታውቋል።

 

በተያያዘ ዜና፣ አሜሪካ ኢራቅን ከወረረችበት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 2003 ጀምሮ 135 ጋዜጠኞች በኢራቅ መገደላቸው ታውቋል። ጋዜጠኞቹ የተገደሉት በጥላቻ፣ በሥራቸው የተነሳ ለመበቀል በማሰብ፣ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በተተኰሰ ጥይት ሊሆን ይችላል ሲል ሲ.ፒ.ጄ. ግምቱን አሥፍሯል።

 

ይሁን እንጂ በድንገተኛ አደጋ (ለምሣሌ በአውሮፕላን፣ በመኪና) እንዲሁም በጤና እክል የተነሳ የሞቱ ጋዜጠኞች እንደማያካትት ይፋ አድርጓል።

 

ከተገደሉት ጋዜጠኞች መካከል 124 ወንዶች፣ 11ዱ ሴቶች ሲሆኑ፣ 113ቱ የኢራቅ ዜግነት ያላቸው፣ 13ቱ አውሮፓውያን፣ 3ቱ የዐረብ ሀገራት ዜጐች፣ 2ቱ የአሜሪካ እንዲሁም 5 የተለያዩ ሀገራት ዜጐች ሲሆኑ፣ አንድ የኢራቅና የስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው መሆኑ ታውቋል።

 

ብዛት ያላቸው ጋዜጠኞች ከተገደሉበት ዓመት 2004 ብልጫውን ሲይዝ፣ 24 ጋዜጠኞች ተገድለውበታል። በ2003 እ.ኤ.አ. 14፣ በ2005 እ.ኤ.አ. 23፣ በ2006 እና በ2007 እ.ኤ.አ. በእያንዳንዳቸው 32 እንዲሁም ዘንድሮ 10 ጋዜጠኞች በኢራቅ ተገድለዋል።

 

ከ135ቱ መካከል 91 ጋዜጠኞች በቀጥታ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ሲገደሉ 44ቱ ደግሞ በተባራሪ ጥይት አልያም በግጭቶች መካከል መገደላቸውን የገለፀው ሲ.ፒ.ጄ. ለ103 ያህሉ ግድያዎች ታጣቂዎች ኃላፊነት መውሰዳቸውን አስታውቋል።

 

ጋዜጠኞቹ በብዛት ከሞቱባቸው አካባቢዎች የኢራቋ መዲና ባግዳድ 74 ግድያዎች ተመዝግበውባት በቀዳሚነት ስትጠቀስ የሞሱል ከተማም 23 ግድያዎች ተመዝግበውባታል።

 

እ.ኤ.አ. በ1981 የተመሠረተው ሲ.ፒ.ጄ. እ.ኤ.አ. ከ1979-89 በተካሄደው የማዕከላዊ አሜሪካ ጦርነት 89 ጋዜጠኞች፣ ከ1955-1975 በተካሄደው የቪየትናም ጦርነት 66 ጋዜጠኞች፣ በኮርያ ጦርነት 17 ጋዜጠኞች፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች 70 ጋዜጠኞች መሞታቸውን የተለያዩ ምንጮችን ጠቅሶ ይፋ አድርጓል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ