በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከአምስት ሺህ በላይ ደርሷል
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ረቡዕ ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
እስካሁን በአዲስ አበባ 3,323 ተጠቂዎች ተገኝተዋል
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 24, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከአምስት ሺህ በላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በወጣው የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ መረጃ፤ 186 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች በመገኘታቸው እስከትናንት 4,848 የነበረው የቫይረሱ ተጠቂዎች፤ በዛሬው ዕለት አምስት ሺህን ተሻግሮ፤ 5,034 ሊደርስ ችሏል።
በዛሬው ሪፖርት መሠረት ሦስት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በመሞታቸው በአገሪቱ በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 78 ደርሷል። በጸና የታመሙ ሰዎች 38 የደረሱ ሲሆን፤ ያገገሙ ሰዎች በ74 ጨምሮ፤ አጠቃላይ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር 1,486 መድረሱ ተገልጿል።
በዛሬው የ24 ሰዓት ሪፖርት መሠረት 186 አዳዲስ ተጠቂዎች የተገኙት 4,034 ለሚኾኑ ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ነው።
ከ186ቱ ሰዎች መካከል 147ቱ ከአዲስ አበባ የተገኙ ሲሆን፤ እስከዛሬው ዕለት ድረስ በአገሪቱ ከተመዘገቡት የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ ከአዲስ አበባ የተገኙት 3,323 ደርሰዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ዕለታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ፤ ከ3,323 ተጠቂዎች ውስጥ ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበባቸው አዲስ አበባ 738፣ ቦሌ 484 እና ጉለሌ 379 መኾናቸው ተጠቅሷል። (ኢዛ)



