በኢትዮጵያ ግዙፉ የዳቦ ማምረቻ ተመርቆ ሥራ ጀመረ
የሜድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረመስቀል (በግራ)፣ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (መሐል)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ (በቀኘ)
9 ሚሊዮን ብር ወጪ ጠይቋል
በሰዓት 80 ሺህ፣ በቀን ሁለት ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም አለው
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 25, 2020)፦ ላለፉት አሥር ወራት በቅርብ ክትትል ሲገነባ የቆየው እና በሰዓት 80 ሺሕ ዳቦ የሚያመርተው የሸገር ዳቦ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ ጀመረ።
በምረቃው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን፤ በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልጽግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ እንዳልነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይ ለሜድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቅቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት ይኾናል በማለት፤ ሜድሮክ ከዚህ ቀደም የነበረበትን ሥራን በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ የማጠናቀቅ ችግር እግረ መንገዳቸውን የተናገሩበት ነበር ማለት ይቻላል።
በቀጣዩ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለውና መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መኾኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መኾኑንም አስታውሰዋል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፤ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገንባቱንም አስታውቀዋል።
የሜድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረመስቀል ደግሞ፤ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል የሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለሥራ ማብቃቱን በመግለጽ፤ ፋብሪካው በ41 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ እንዳረፈ፤ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺሕ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በስድስት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺሕ ዳቦ የሚያመርት መኾኑን እና በቀን በሦስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊዮን ዳቦ የሚያመርት እንደኾነም ተገልጿል።
ፋብሪካው በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ መኾኑን፣ አጠቃላይ ወጪውም በሜድሮክ እኅት ኩባንያዎች የተሸፈነ እንደኾነም ከአቶ አብነት ንግግር ለመገንዘብ ተችሏል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሒደት ቁጥራቸውን 3 ሺሕ 400 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። (ኢዛ)



