ሞ ኢብራሂም የአፍሪካን የመልካም አስተዳደር ሪፖርት ይፋ ያደርጋሉ

Dr. Mo IbrahimEthiopia Zare (እሁድ መስከረም ፳፭-25 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 5, 2008)፦ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ነገ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2001 ዓ.ም. የአፍሪካ ሀገሮችን የመልካም አስተዳደር ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ ሊያደርግ ነው። 

 

በአፍሪካ የመሪዎች ሽግግር ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድና ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለሚለቁ የአፍሪካ መሪዎች፣ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት በመስጠት የተቋቋመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፣ ነገ ሰኞ ይፋ የሚያደርገው የአፍሪካ ሀገሮች የመልካም አስተዳደር ኢንዴክስ፣ ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገሮች ወቅታዊ የመልካም አስተዳደር ደረጃቸውን ሊያሳይ በሚችል መልኩ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።

 

የሞ አብራሂም ፋውንዴሽን በዋነኝነት ሁለት ዓላማዎችን ተግባራዊ የማድረግ ውጥኑን ለማሳካት፣ ባለፈው ዓመት በአፍሪካ ሥልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ለለቀቁ መሪዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት በወሰነው መሠረት እ.ኤ.አ. የ2007 ዓ.ም. ተሸላሚ ያደረጋቸው የቀድሞውን የሞዛምቢክ መሪ ጂ አኪም ቺሻኖ መሸለሙ ይታወቃል።

 

ፋውንዴሽኑ ለጂ አኪም ቺሻኖ የ5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሰጥቷቸዋል። ሽልማቱ በ10 ዓመት ውስጥ በየዓመቱ እየተሰጠ የሚጨረስ ሲሆን፣ ተሸላሚ መሪዎች በተጨማሪ ስማቸውን በመጠቀም ለበጎ ተግባር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጤታማ ከሆኑ የ200ሺ ዶላር ሽልማት ይሰጣል።

 

ዘንድሮ ይፋ የሚደረገው የአፍሪካ ሀገሮች የመልካም አስተዳደር ሪፖርት የተጠናከረው ፋውንዴሽኑ ባቋቋመው ቦርድ ሲሆን፣ በቦርዱ ውስጥ በአባልነት ከሚገኙ ታዋቂ ግለሰቦች መካከል የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን፣ የቀድሞው የአየርላንድ ፕሬዝዳንትና በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩ ሚስስ ሜሪ ሮቢንሰን፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ዋና ፀሐፊ የነበሩትና የታንዛኒያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሳሌም አህመድ ሳሌም ይገኙበታል።

 

ሪፖርቱ ይፋ በሚደረግ ዕለት የፋውንዴሽኑ መሥራች ሞ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች እንግዶችም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

ሰኞ ይፋ የሚደረገው የሞ ፋውንዴሽን የገቨርናንስ ሪፖርት ለማዘጋጀት ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገሮች ብሔራዊ ይዘትን በመገምገም የሚነሣና 58 መመዘኛዎችን ይጠቀማል።

 

የአፍሪካ ሀገሮች ያሉበትን የመልካም አስተዳደር ደረጃ በተሟላ መልኩ ለማቅረብ፣ ሪፖርቱ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነው። እነዚህ ዋና ዋና ክፍሎች ጥንቃቄና ደህንነት፣ የሕግ የበላይነትና ግልፅነት፣ ሙስና፣ አሣታፊነት፣ የሰብዓዊ መብት፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት እና የሰው ሀብት ልማት ናቸው።

 

ኢንዴክሱ መመዘኛዎቹን የተጠቀመባቸው መንግሥታት ለዜጎቻቸው የሚሰጡት አገልግሎትን በተመለከተ እውነታውን ለማስቀመጥ ነው። በአጠቃላይ የሪፖርቱ ውጤት ዋና ምልከታ የመንግሥታት አሠራርና ይዘት ለማሳወቅ ነው።

 

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ይዞት የተነሳው ዓላማ ደጋፊና ተቃዋሚም ያገኘ መሆኑን ሪፖርቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ በፍቃዳቸው ሥልጣናቸው ለሚለቁ መሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ መሸለም ጉቦ ከመስጠት አይተናነስም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ በተቃራኒው የፋውንዴሽኑ ዓላማ አፍሪካ ከእርስ በእርስ ግጭት እንድትወጣና የመሪዎች የሥልጣን ሽግግር ሠላማዊ እንዲሆን የራሱ ድርሻ አለው በማለት ይገልጻሉ።

 

የፋውንዴሽኑ የመጀመሪያ የመልካም አስተዳደር ሪፖርት አዲስ አበባ እንዲሆን የተመረጠው ከተማዋ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት የሚገኝባት በመሆኑ ነው። የፋውንዴሽኑ ሪፖርት ይፋ ሲሆን ይዞት የሚወጣው የመልካም አስተዳደር ውጤት ከአሁኑ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ሊፈጥር ይችላል የሚለው ግምት የላቀ ነው።

 

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን መሥራች በትውልድ ሱዳናዊ ሲሆኑ፣ ሞ በመላው ዓለም በኢንቨስትመንት የተሠማሩና በአፍሪካ በሞባይል ሽያጭ ትልቅ ድርሻ ያለው የሴልቴል ኢንተርናሽናል ባለቤት ነበሩ። ሞ ኢብራሂም ይህንን የቴሌኮም ኩባንያ በ3.4 ቢሊየን ዶላር በቅርቡ መሸጣቸው ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ