ዲቪ 2010 ተጀምሯል

Ethiopia Zare (ሰኞ መስከረም ፳፮-26 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 6, 2008)፦ የአሜሪካን ኤምባሲ እ.ኤ.አ. የ2010 ዓ.ም. የዲቪ ሎተሪ አመልካቾች ማመልከቻቸውን ከኦክቶበር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. (መስከረም 21 ቀን 2001 ዓ.ም.) ጀምሮ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን አስታወቀ።

 

አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ረቡዕ በጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፣ የአሜሪካን ኤምባሲ ከእንግዲህ በኋላ 10+2 ለዲቪ ማመልከቻ የትምህርት መመዘኛ የብቃት ማስረጃ አድርጎ እንደማይቀበል አስታውቋል።

 

በአሜሪካ ኤምባሲ የኮንሱላር ምክትል ኦፊሰር ሚስስ ሂተር ጉይሞንድ በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ እንደገለፁት፣ የዘንድሮው 2010 የዲቪ ሎተሪ የትምህርት መመዘኛ ብቁ ለመሆን አመልካቾች በኤምባሲው ከተቀመጡት ማስረጃዎች፤ አንዱ የግዴታ ሊኖራቸው ይገባል። የዲቪ ማመልከቻው ወቅት ለሁለት ወራት ይቆያል ተብሏል።

 

ለዲቪ አመልካቾች የቀረቡ መመዘኛዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት (12ኛ ክፍል) መልቀቂያ ሠርተፊኬት 5 ወይም ከዚያ በላይ የትምህርት ዓይነቶችን ያለፉበትን የሚያሳይ፣ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሠርተፊኬት እና የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ሠርተፊኬት፣ ከ2ኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ያገኙት የሙያ ትምህርት ዲፕሎማ (10+3) ወይም ከኢትዮጵያ የጦር አካዳሚ የተመረቁበት መረጃ የሚያሳዩ መሆን ይኖርባቸዋል።

 

ኤምባሲው የተሟላ የሥራ ልምድ ተብሎ ተቀባይነት የሚኖረው የሁለት ዓመት የኮሌጅ ሥልጠና ወይም ልምድ ለሚጠይቅ ሥራ ባለፉት አምስት ዓመታት በቋሚነት ቢያንስ ሁለት ዓመት የሠሩ ብቻ መሆኑን ጠቁሟል።

 

የዲቪ አመልካቾች ለዲቪ አመልክተው ግን ቪዛ ቢከለከሉ ለማመልከቻ የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ ስለማይሆን፣ አመልካቾች የማመልከቻ ፎርሙ በሚጠይቀው መሠረት እንዲሞሉ ኤምባሲው ጠይቋል።

 

በዲቪ ማመልከቻ ላይ የመጀመሪያ ማመልከቻውን ሲሞሉ ባለቤትዎን (ሚስት ወይም ባል) እና ከ21 ዓመት በታች የሆኑና ያላገቡ ልጆችን ስም ማስፈር የሚገባ መሆኑን የገለፀው የኤምባሲው መግለጫ፣ በፎርሙ ላይ ባለቤትዎ ከእርስዎ በፊት ከነበራቸው ጋብቻ የወለዷቸውን ልጆችና በሕጋዊ መንገድ በማደጎ የተረከቧቸውን ልጆች ይጨምራል ሲል ገልጿል።

 

የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የሱማሊያ ዜጋ የሆኑ የዲቪ አመልካቾችን በሚመለከት የትምህርትና የሥራ ማስረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚቸገር በመሆኑና እነዚህ ማስረጃዎች ሳያረጋገጥ ደግሞ የቪዛን ጉዳይ ለመስፈፀም ያስቸግራል ብሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ