Water flows through Ethiopia's Grand Renaissance Dam as it undergoes construction work on the river Nile in Guba Woreda, Benishangul Gumuz Region, Ethiopia. (Reuters)

በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ሲሞላ፤ ጉባ ወረዳ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (ፎቶ፣ ሮይተርስ)

በ78 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ቢባልም፤ አሁን 160 ቢሊዮን ብር ይጠይቃል ተብሏል
እስካሁን 120 ቢሊዮን ብር ፈጅቷል

ኢዛ (ሐሙስ ነኀሴ ፲፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 20, 2020)፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ወጪ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስና እስካሁን 120 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው ዛሬ ሐሙስ ነኀሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ለህዳሴ ግድብ የቦርድ አመራሮችና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በግድቡ የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ በቀረበ ሪፖርት ላይ ነው።

በዚሁ መድረክ ላይ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፤ የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱንና እስካሁን ለግድቡ 120 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት የግድቡ ሥራ ሲጀምር ይጠናቀቅበታል ተብሎ የተሰላው በጀት 78 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሒደት 120 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

በውይይት መድረኩ ላይ፤ ግንባታው በ2015 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ አጠቃላይ የግድቡ ወጪ 160 ቢሊዮን ብር የሚደርስ መኾኑ ተገልጿል።

በቀረበው ሪፖርት መሠረት የግድቡ ወጪ መጀመሪያ ይጠናቀቅበታል ተብሎ ከተያዘው በጀት ከእጥፍ በላይ ዋጋ የሚጠይቅ መኾኑን ነው።

“ግድቡ የነፃነታችን ዓርማ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀጣይ ዓመት ሥራዎችን ማሳካት ላይ ማተኮር ይገባዋል ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ግለሰብም ኾነ ኃይል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ እንደቆመ እንደሚቆጠር በዚሁ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ