ጸጋ ንጉሴ

Hailemariam Desalegn and Salva Kiir Mayardit

ባሳለፍነው ሳምንት ከዚህ ቀደም እጅና ጓንት ሆነው ይታዩ የነበሩት ጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ሰንብተዋል።

የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳትን ሳልቫ ኪር በትጥቅ ትግል የተሰማሩ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ቢሮዋቸውን በጁባ እንዲከፍቱ ፍላጎት አሳይተዋል የሚለው ዘገባ ከወጣ በኋላ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ውጥረት ተፈጥሮ ነው ሳምንቱ የተገባደደው።

ምንም እንኳ ሳልቫ ኪር የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በአገራቸው ለማስጠለልና እንዲሁም ቢሮዋቸውን በዋና ከተማቸው እንዲከፍቱ መፍቀዳቸው በኦፊሴል የተነገረ ነገር ባይሆንም፤ ከዚህ ወሬ መራገብ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል በተከታታይ የተሰጡት መግለጫዎች ነገሩ እንዲህ ቀላል እንዳልሆነ አመላካች ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የደቡብ ሱዳኑን አምባሳደር ከአገር እንዳባረረ በዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኀን ሳይቀር የተዘገበ ሲሆን፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል ጥርት ብለው ያልወጡ መግለጫዎች ሲሰጡ ሰንብተዋል።

የሳልቫ ኪር ግብጽን ጎብኝቶ መመለስ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ዘንድ ስጋትን እንዲሁም ጥርጣሬን ማጫሩ ከግብጽ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎረቤት አገራት የሚደረገው ሽርጉድ በቂ ሰበብ እንደሆነ ይገመታል።

ምንም እንኳ ግብጽና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ሳቢያ አንድ ጊዜ ረገብ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እየጋለ የሚመጣው የቃላት ጦርነታቸው ወደ ከፋ አለመስማማት ውስጥ ባይከታቸውም፤ ሁለቱም አገራት በየፊናቸው በሚያደርጓቸው ዓለማቀፍ ግንኙነቶች በጥርጣሬ እንደተያዩ ነው።

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ከጥቂት ወራት ወዲህ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት የሆኑ መሪዎችን ሲያነጋግሩ ሳልቫ ኪር ሦስተኛው ናቸው።

በጥቅምት ወር መግቢያ ላይ ወደ ካይሮ ብቅ ያሉትና ከአገራቸው እግራቸው ሲወጣ ብዙም የማይታዩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከግብጹ አቻቸው ጋር በቀጠናው የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችና ስምምነቶች አድርገው መመለሳቸው አይዘነጋም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከቆየው ጸቧ ባሻገር ለኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ቡድኖች ድጋፍ መስጠቷ ለኢትዮጵያ ደህንነት ስጋት መሆኗን መንግሥት በተደጋጋሚ የሚገልጸው ነገር ነው።

ኢሳያስ አፈወርቂን ያነጋገሩት አል ሲሲ በቀጣዩ ወር ደግሞ ወደ ኡጋንዳ ሻገር ብለው ዩዌሪ ሙሶቬኒንም አነጋግረው ተመልሰዋል።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ ከካይሮ ጉብኝት መልስ የሳልቫ ኪር ንግግር ከኢትዮጵያ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ቢከታቸው የሚገርም አይሆንም።

ከዚህ በዘለለ ደግሞ የደቡብ ሱዳን የውሀና የመስኖ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ሰው፤ "ኢትዮጵያ ግብጽን ሳታማክርና የግብጽን ይሁንታ ሳታገኝ የአባይን ግድብ ለመሥራት መነሳቷ እጅግ ጥፋት ነው" ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፤ በተለይም በአባይ ተፋሰስ አባል አገራት መካከል እርስ በእርስ ጥርጣሬ እንዲሁም አለመግባባት እንዲፈጠር ሰበብ ሆናለች ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት መሰንዘራቸው፤ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በእጅጉ መሻከሩን ያመለክታል።

ነጻነቷን አግኝታ እንደ አገር ከቆመች ሁለት ሻማ እንኳ ሳትለኩስ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ የተዘፈቀችው ደቡብ ሱዳን በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎቿን በሞት ስታጣ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ አገር ጥለው እንዲሰደዱ ሆነዋል።

በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን ሸሽተው የሚኮበልሉ ደቡብ ሱዳናውያንን በመቀበል ያስጠለለ ከመሆኑም በላይ፤ ሳልቫ ኪርን ከባላንጣቸው ሬክ ማቻር ጋር ለማደራደር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ህልቆ መሳፍርት የሚባሉ ውይይቶችና ድርድሮች የተካሄዱበት የሁለቱን ኃይሎች አቋም ወደ አንድ ለማምጣት በተደረገው ጥረት እንደምንም ሬክ ማቻርና ጦራቸው ወደ ጁባ እንዲመለስና እሳቸውም የምክትል ፕሬዚዳንትነቱን ወንበር እንዲይዙ ያስቻለ ቢሆንም የማታ ማታ የታየችውን የተስፋ ጭላንጭል አጥፍተውት ባለፈው ሀምሌ ወር ላይ ዳግም ወደማያበቃው ጦርነት ተመልሰዋል።

ይህ ሁሉ አበሳ ያለባቸው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ይልቅ የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች መምረጣቸው ነገሩ በግብጽ በኩል ምን ያህል እንደተገፉ ያሳየ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግን አለኝ የሚለውን የጎረቤት አገራት ጥብቅ ወዳጅነት ፈተና ላይ የጣለ ሆኗል።

ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ የለየለት የጠላትነት መፈራረጅ ውስጥ ከገባበት የኢሳያስ መንግሥት በስተቀር፣ ለ25 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በኦፊሴል ለመደገፍ የተነሳ የጎረቤት አገር ባለመኖሩ የደቡብ ሱዳን መንገድ አጣብቂኝ ውስጥ ሳይከተው እንደማይቀር የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

እውን ሳልቫ ኪር አሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለሚያራምዱት አዲስ አቋም ግብጽ ከጀርባቸው ትኖር ይሆን? እንዳሉትስ ለኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ቡድኖች አዎንታዊ ቃላቸውን ያጸኑት ይሆን? የኢትዮጵያ መንግሥትስ ይህን የወደቀበትን አስደንጋጭ የደቡብ ሱዳን አቋም ለማስቀየር የተለየ የፖለቲካ አቅጣጫ ይቀይስ ይሆን? ይህን አብረን የምናየው ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!