የትግራይ ክልል አካሒደዋለሁ ያለው ምርጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ተባለ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት
ምርጫው ቢደረግ፤ የማይጸና መኾኑንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወሰነ
ኢዛ (ቅዳሜ ነኀሴ ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 5, 2020)፦ የትግራይ ክልል አካሒደዋለሁ ያለው ምርጫ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ መኾኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ቅዳሜ ነኀሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ መንግሥት አካሒደዋለሁ ያለው ምርጫ ቢደረግ እንኳን፤ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዳልተደረገ የሚቆጠር፤ የማይጸናና ተፈጻሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት በሙሉ ድምፅ መጽደቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ ፕሬስ መግለጫ
አዲስ አበባ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ነኀሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው 5ኛ ዙር የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ወደ ጎን በመተው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 እና አዋጁን መሠረት አድርጎ ያቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን፣ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና የፈጸማቸው ተግባራት የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔ እንዲሰጥበት በሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተጣርቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለምክር ቤቱ በሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች በኩል በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱም ላይ በእስከ አሁኑ ሒደት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር ያለው መኾኑንና ሕገወጥ አካላት በሚፈጽሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን መኾኑ እና በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።
በሌላ በኩል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ የትግራይ ክልል እያካሔደ ካለው ሕገወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው መኾኑ ከማስቀመጡም ባሻገር፤ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ በደብዳቤ ሕገ መንግሥቱና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሰጡትን ማሳሰቢያ አለመቀበሉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሏል ምክር ቤቱ።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሚከተሉትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች በሙሉ አጽድቋል።
1) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2)(መ) ጋር ይቃረናል፤
2) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012ን መሠረት አድርጎ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ሥልጣን ይጥሳል፤
3) የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት፣ አስፈጻሚ አካላት እና የምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈጸሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ በመኾናቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይጸኑ እና ተፈጻሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የመጨረሻ ውሳኔ አስተላልፏል።



