አስገራሚው የሕፃኗ ቀዶ ጥገና በአዲስ አበባ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መስከረም ፳፰-28 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 8, 2008)፦ ወ/ሮ መስከረም አሰግድ ይባላሉ። ጭድና ጭቃ በመቀላቀል ውበት ያላቸው የአርት ሥራዎችን በቤቱ ውስጥ ከሚሠራው አርቲስት ኤሊያስ ጋር ሠንበሌጥ ሣር ፍለጋ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ቱሉ ኮርማ ተራራ በከታ ወረገኑ ገጠር ገበሬ ማኅበር ያመራሉ።
ሠንበሌጥ ሣር ለመግዛት በቦታው የተገኙት ወ/ሮ መስከረም ከሁለት ዓመቷ ሕፃን አያት በተሰባበረ አማርኛ ተማጽኖ ይቀርብላቸዋል። ጉዳዩ ምን እንደሆነ ሲጠይቁም፤ የሕጻኗ አያት ወ/ሮ ደማ ዳዲ፤ ልጃቸው ሕፃን ታሪኳ ቦቼን ስትወልድ ሕይወቷ ያልፋል። ሕፃኗም በተወለደች በስድስት ወሯ ከእህቷ እጅ ላይ በመውደቋ በጭንቅላቷ ላይ የመጎድጎድ ምልክት በማየታቸው ደብረ ዘይት በሚገኘው ቢሾፍቱ ሆስፒታል ሲወስዷት ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ይባላሉ። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደግሞ የአንድ ዓመት ቀጠሮ ይሰጣቸዋል።
ለወ/ሮ መስከረም ይህን ካጫወቷቸው በኋላ የሚያውቁት ሰው ካለ የቀጠሮውን ቀን እንዲያሳጥሩላቸው ይጠይቃሉ። አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር የኾነውን የሂሮሎጂ ስፔሻሊስት ዶ/ር ዮናስ ዘገየን በአጋጣሚ ያገናኟቸውና ስለ ሕፃን ታሪኳ ጉዳይ አስረድተው የሚያውቁት ሰው ካለ እንዲረዷቸው ይጠይቃሉ። ዶ/ር ዮናስ ሕፃኗን ሄደው ለማየት ፈቃደኝነታቸውን በመግለጻቸው አብረው ወደ ደብረዘይት ይሄዳሉ።
ዶ/ር ዮናስ ስለሕፃኗ ሕመም እንደገለጹት፤ “በጭንቅላት ውስጥ የሚመነጭ ውሃ ሲበዛ እየተጨመቀ ጭንቅላትን ትልቅ ያደርጋል። ይህ ጉዳት ደግሞ ወደፊት ዘገምተኛ ያደርጋል።” ዶ/ር ዮናስ ሕፃኗን ካዩ በኋላ፤ ሕፃኗን በቀዶ ሕክምና መርዳት እንደሚችሉ ነገር ግን ሕክምና መስጫ ቦታ እንደሌለ ይገልጻሉ። ለዚህ አገልግሎት የሚሆን ቦታ ሲያፈላልጉም ቤተል ሆስፒታል ተባባሪ ይሆንላቸዋል።
ሕፃኗ ሆስፒታል ከገባች በኋላ ለአንዳንድ አገልግሎቶች ወጪ የሚሆን 3ሺ 500 ብር እንደሚያስፈልግ ይነገራቸዋል። ወ/ሮ መስከረም ከራሳቸው 1ሺህ ብር፣አርቲስት ኤሊያስ 1ሺህ ብር፣ አንድ ሌላ ጓደኛቸው ደግሞ 1ሺህ ብር ሲያዋጡ ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ መጥታ የነበረች ሌላ ግለሰብ 500 ብር በማዋጣት ትብብር አደረጉላት።
ዶ/ር ዮናስ በበኩላቸው ቀዶ ጥገናውን ሊያደርጉ አንድ ቀን ሲቀራቸው አሜሪካን ሀገር ያለው ልጃቸው የመኪና አደጋ እንደደረሰበት ይነገራቸዋል። ቀድሞውኑ የሕፃኗን ሕይወት ለማዳን ቃል ገብተው ነበርና እንደምንም አድረው ኀሙስ መስከረም 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና አድርገውላታል።
ዶ/ር ዮናስ ስለቀዶ ሕክምናው ሲገልጹ፤ “በጭንቅላቷ ውስጥ የተጠራቀመው ፈሳሽ እንዲወገድ ለማድረግ ከጭንቅላቷ ጀምሮ በጀርባዋ በኩል ውስጥ ለውስጥ ቲዩብ ይገባላትና ከፍሳሽ ማስወገጃዋ ጋር እንዲገናኝ ይደረጋል። ስለዚህ ፈሳሹ በጭንቅላቷ ከመጠራቀም ይልቅ በዛ በኩል ይወገዳል። ቲዩቡም ምናልባት እያደገች ስትሄድ አጥሮ እንዲቀየር ካልተደረገ በስተቀር በሕይወት እስካለች አብሯት ይኖራል” ብለዋል።
በአሜሪካ ፍሎሪዳ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የአዕምሮ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶ/ር ዮናስ ቀዶ ሕክምናውን ከጨረሱ በኋላ ወደ አሜሪካ ልጃቸው ጋር አቅንተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ መሣሪያውን ወይም ቲዩቡን ካገኙ ቀዶ ሕክምናውን የሚሰጡ ዶክተሮች መኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር ዮናስ ለወደፊቱም በሃይድሮ ሲፋለስ በሽታ የተያዙ ሕሙማንን ለማከም የሚቻልበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ቃል ገብተዋል።
ሕፃን ታሪኳ ከአያቷ ጋር በወ/ሮ መስከረም ቤት ትገኛለች። ቁስሉ እስኪደርቅላት በተመላላሽ ነርስ ክትትል እየተደረገላት ነው። በአሁን ሰዓትም በሙሉ ጤንነት ላይ ትገኛለች።



