የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ (በግራ)፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድና ኮሮና ቫይረስ

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ (በግራ)፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድና ኮሮና ቫይረስ

ፓርላማው ጉዳዩ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል

ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 18, 2020)፦ ዛሬ ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ አጭር ሪፖርት ያቀረቡት የጤና ሚኒስትሯ፤ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ተንተርሶ ተገቢውን ጥንቃቄና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ምርጫ ማካሔድ የሚቻል ስለመኾኑ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ ኮቪድ 19 መከላከልን ከግምት ያስገባ የምርጫ ሥነምግባር፣ ደንብና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት አገራዊ ምርጫ ማካሔድ ይቻላል ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት እየሠፋ መኾኑ የሚታይ ቢኾንም፤ የመከላከል አቅምን በማጎልበትና በመጠንቀቅ፤ የምርጫ ሒደቱን ማካሔድ የሚቻል ስለመኾኑ አንደምታ ያለው ሪፖርታቸው፤ ከዚህ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው የሚጠቁምም ነው።

አገራዊ ምርጫውን ለማካሔድ የመከላከል አቅምን በማጎልበት፤ በተጨማሪ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት፤ ምርጫውን ማካሔድ የሚቻል መኾኑን ጠቁመዋል።

በሪፖርታቸው ቅድመ ሁኔታዎች ብለው ካመለከቱት ውስጥ አንዱ ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሒደት በተለየ መልኩ ኮቪድ 19ን መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ሥነምግባር፣ ደንብ እና ማስፈጸሚያ መመሪያዎች ማዘጋጀትና በተዘጋጁት ዝርዝሮች መሠረት በሁሉም ደረጃ በበቂ ዝግጅት ወደ ትግበራ መግባት ያስፈልጋል የሚል ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ሒደት ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የኾነ የወረርሽኝ ሥርጭት ከተከሰተ በተለየ ሊያስፈልገው ስለሚቻል ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀት ያስፈልጋል የሚል ነው።

በዚህ ሪፖርት ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ውይይት በማድረግ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!