PM Abiy Ahmed answering questions in parliament

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለጥያቄዎች ምላሽ ሲሠጡ

“በኢትዮጵያ ሰላምና ሕልውና ላይ ከመጣ እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም” ዶ/ር ዐቢይ

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 22, 2019)፦ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ሚዲያዎችን የሚመለከት ነበር። የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሞያው ከሚፈቅደው ውጭ ከሚዛናዊነት ርቀው የሚሠሩ ሚዲያዎች እየተስተዋሉ ነውና፤ ምን ታስቧል የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ ነው።

በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የሠጡት ምላሽ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ነበር። በተለይ በውጭ ዜግነት ባላቸው የሚዲያ ባለቤቶች ላይ ባነጣጠረው መልሳቸው እንዲህ ብለዋል፤ “በተለይ የውጭ አገር ዜጋ የኾናችሁ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፣ ስትፈልጉና ሰላም ሲሆን፣ እዚህ ተጫውታችሁ እኛ ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሔዱበት አገር ያላችሁ ሰዎች፤ ትእግሥት እያደረገን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው” በማለት ገልፀዋል።

አያይዘውም፤ “በማንኛውም ሰዓት በኢትዮጵያ ሰላምና ሕልውና ላይ ከመጣ አማርኛ ብትናገሩም፣ ኦሮምኛም ብትናገሩም እርምጃ መውሰዳችን የማይቀር መኾኑን በጥንቃቄ መገንዘብ አስፈላጊ ይኾናል” ብለዋል።

ከሚዲያ አሠራር ጋር ተያይዞ የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ አክለው እንደተናገሩት፤ “ሁለት ቤት መጫወት አይቻልም፤ እኛ የምንሔድበት አገር የለንም አገራችን ይሔ ስለኾነ ሰላም እንፈልጋለን” በማልት ቅያሪ (አገር) ያላችሁ በነፃነት ስም አትነግዱ የሚል ምላሽ ሠጥተዋል።

ዴሞክራሲን ብታግዙ እሰየሁ! ካልኾነ ግን በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም የማይቀለድ ስለመኾኑም አሳስበዋል። በዚሁ ጥያቄ ላይ ሚዲያዎች ነፃነትን በአግባቡ መጠቀም ላይ ችግር እንዳለም በመጠቆም፤ “ችግሩም አንደኛው ሚዲያ የነጋዴዎች መቀለጃ መኾኑ ነው” ብለዋል።

ይህንንም ሲያብራሩ፤ “የዘር ነጋዴዎች፣ የሃይማኖት ነጋዴዎችና የብር ነጋዴዎች መቀለጃ መኾኑ ነው” ብለዋል።

በዚህ ዐይነት መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች የኾነ አካል ወክያለሁ ብሎ፤ ከዚያ አካባቢ የሚገኝ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንደኾነም በምላሻቸው ጠቅሰው፤ እንዲህ ዐይነቱን ችግር ለመቅረፍ ሕዝቡም የራሱ ኃላፊነት አለበት ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ