Jawar Mohammed (L), Bekele Gerba (M) and Federal Attorney General

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ) እና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓርማ (ከጀርባ)

የፊታችን ሰኞ መስከረም 11 ቀን ክሱ ይደርሳቸዋል

ኢዛ (ቅዳሜ መስከረም ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 19, 2020)፦ እነአቶ ጃዋር መሐመድ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅና ሌሎች አዋጆችን በመተላለፍ በፈጸሙት ወንጀል ተደራራቢ ክሶች እንደተከፈተባቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው የዓቃቤ ሕግ መረጃ፤ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24 ሰዎች፤ አሥር ተደራራቢ ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ክስ መሥርቷል።

እንደ ዓቃቤ ሕግ የዛሬው መረጃ፤ እነአቶ ጃዋር መሐመድ የፊታችን ሰኞ መስከረም 11 ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ይደርሳቸዋል።

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተደራራቢ ክሶች ከመሠረተባቸው 24 ሰዎች መካከል፤ ሃምዛ አድናን፣ ጃዋር ሲራጅ፣ በቀለ ገርባ ይገኙበታል። ከዚህም ሌላ በሌሉበት የተከሰሱት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN)፣ ደጀኔ ጉተማ፣ ብርሃነመስቀል አበበ ይገኙበታል።

24ቱ ተከሳሾች ከተመሠረቱባቸው ክሶች መካከል፤ በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በእርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ የሚለው አንዱ ነው።

ከዚህም ሌላ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ፤ እና የጦር መሣሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ተመሥርቶባቸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ