እነአቶ ጃዋር መሐመድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲሔዱ ትእዛዝ ተሰጠ
አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ)
ጠበቆች ማረሚያ ቤት አይውረዱ ብለው ተከራክረው ነበር
ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 24, 2020)፦ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ የተመሠረተባቸውን ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። በዚህ መዝገብ የተከሰሱ ግለሰቦች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ኾነው እንዲከታተሉም ታዝዟል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን ትእዛዝ የሰጠው በዚህ መዝገብ የተጠቃለሉት 18ቱም ተከሳሾች ክስ ስለተመሠረተባቸው፤ የተሻለ አያያዝ ወዳለበት ማረሚያ ቤት ሔደው ጉዳያቸውን መከታተል እንደሚችሉ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፤ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ማረሚያ ቤት ኾነው ጉዳያቸውን ይከታተሉ ብሎ ትእዛዝ ሰጥቷል።
በዚህ ውሳኔ ላይ ግን የተከሳሾቹ ጠበቆች ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፤ በተለይ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሃምዛ አድናን ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ስለኾኑ፤ አሁን ባሉበት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ መቆየት አለባቸው የሚል ነው።
ሌሎቹም ተከሳሾች አሁን ባሉበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ክሱ እስኪነበብ እንዲቆዩ ጠበቆቹ ጠይቀዋል።
ጠበቆቹ ላቀረቡት ጥያቄ ምላስ የሰጠው ዓቃቤ ሕግም፤ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መኾኑን አስታውሶ፤ ሌሎች ክስ የተመሰረተባቸው ወደ ማረሚያ ቤት ሲወርዱ፤ እነዚህ ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት የማይወርዱበት አንዳችም ምክንያት የለም በሚል ተከራክረዋል።
የሁለቱን ወገኖች ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤትም የተሻለ አያያዝ ያለው በማረሚያ ቤት በመኾኑና ሕጉም ክስ የተመሠረተበት ማንኛውም ተከሳሽ ማረሚያ ይውረድ ስለሚል፤ ሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ (ሐሙስ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) ጀምሮ ወደ ማረሚያ ይውረዱ በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል።
በዚህ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸውና ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሦስት ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርሳቸውና እንዲቀርቡም ፍርድ ቤቱ አዝዟል። ከዚህም ሌላ ፍርድ ቤቱ ክስ ለመስማትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)



