Hachalu Hundessa

አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ

የተጠቀሰውን ወንጀል አልፈጸምንም በማለት ቃላቸውን ሰጡ

ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 14, 2020)፦ በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ክስ የተመሠረተባቸው አራት ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ የሌላቸው መኾኑንና ክስ የተመሠረተባቸውን ወንጀል አልፈጸምንም አሉ።

ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ አራቱ ተከሳሾች ይህንን ያሉት ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀጠሮ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ነው።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎን በተመለከተ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመረጃ ገጽ ላይ እንዳሰፈረው፤ በዛሬው ቀጠሮ መሠረት ተከሳሾች በተመደበላቸው ጠበቃ አማካኝነት በቀረበባቸው ክስ ላይ ምንም የክስ መቃወሚያ የሌላቸው መኾኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

ይኸው መረጃ አያይዞም፤ ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፤ እያንዳንዳቸው ተከሳሾች በክሳቸው ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል አልፈጸምኩም በማለት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል።

የተከሳሾቹን ምላሽ ያደመጠው ፍርድ ቤትም፤ የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ቃል ለመስማት ለኅዳር 23፣ 24 እና 25 ቀነ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን ችሎት ማጠናቀቁን ይኸው የዓቃቤ ሕግ መረጃ ያስረዳል።

በአርቲስት ሐጫሉ ግድያ በዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው ጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ ዓለማየሁ እና ላምሮት ከማል ናቸው።

ከአራቱ ተከሳሾች ሦስቱ አቅም የሌላቸው መኾኑን በመግለጽ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀው የነበረ ሲሆን፤ አራተኛዋ ተከሳሽ ላምሮት ከማ ደግሞ ጠበቃ በግሌ የመቅጠር አቅሙ ቢኖረኝም፤ ፍቃደኛ ኾኖ ጥብቅና የሚቆምልኝ ሰው ማግኘት ባለመቻሌ፤ ጠበቃ ይመደብልኝ በማለት ጠይቀው የነበረ በመኾኑ፤ በመንግሥት ጠበቃ ተመድቦላቸው ፍርድ ቤት መቅረባቸውም ተጠቅሷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ