ESAT

ኢሳት

ችግሩ የፋይናንስ እጥረት ነው

ኢዛ (ቅዳሜ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 17, 2020)፦ በሳተላይት የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሚተላለፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአድማጭ ተመልካች ከሚዘወተሩት መካከል አንዱ በመኾን የሚታወቀው የኢሳት ሥርጭት መቋረጥ አነጋጋሪ ኾኗል።

የፊታችን ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. አሥራ አንደኛ ዓመቱን የያዘው ኢሳት ከትናንት ጀምሮ ሥርጭቱ ስለመቋረጡ ጣቢያው አስታውቋል።

የኢሳት ሥርጭት መቋረጥ ከዚህ ቀደም እንደኾነው በመንግሥት እርምጃ እና በቴክኒክ ችግር ሳይኾን፤ ከፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዘ ስለመኾኑ ጠቋሚ መረጃ ተሰጥቷል።

በአሥራ አንድ ዓመታት ጉዞው በተለይ ከሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ዜጐች የጣቢያው ሥርጭት እንዳይቋረጥ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ቢኾንም፤ አሁን ግን ይህ የፋይናንስ ድጋፍ በመቀዛቀዙ ሥርጭቱን ለመቀጠል እንዳላስቻለው እየተገለጸ ነው።

ከኢሳት መቋረጥ ጋር በተያያዘ የጣቢያው ጋዜጠኞች ከሰጡት ማብራሪያ መገንዘብ እንደተቻለውም፤ ለሳተላይት የሚከፈለው ክፍያ መወደድና አሁን ባለው ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኢሳት የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች ከመቀዛቀዝ ጋር የተያያዘ ነው።

በአንጻሩ በተለይ ከለውጡ ወዲህ በይበልጥ ደግሞ ከቅርብ ወራት ወዲህ ኢሳት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በቀጥታ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጭምር በማነጋገር የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ጣቢያውን በተለየ እንዲታይ እያደገው እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ።

አሁን ግን በፋይናንስ እጥረት ሥርጭቱ መስተጓጐሉ እንዴት? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ሲሆን፤ የገጠመውን ችግር ለመፍታት እያጋጠመው ያለውን ችግር ቀድሞ በማሳወቅ መፍትሔ ለማበጀት እንዴት እንዳልቻለም ግራ ያጋባል የሚሉ ወገኖች አሉ።

በአገሪቱ ሚዲያ ታሪክ ከለውጡ በፊትም ኾነ አሁን ለመረጃ ከሚመረጡ ጣቢያዎች መካከል በአማራጭነት የሚታይ ጭምር በመኾኑ የጣቢያውን ሥርጭት ለማስቀጠል ጣቢያውን የሚመሩ ኃላፊዎች መፍትሔ መፈለግ ይገባቸው እንደነበር የሚጠቁም አስተያየት ሰጪዎች፤ እንደ ኢሳት ያሉ ጣቢያዎች እንዲህ ባለ ሁኔታ መቋረጣቸው አንድ ጉድለት ስለመኾኑም ያመላክታሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ