የአገሪቱ ባንኮች አንድ ትሪሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ሰበሰቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት
ባንኮች ካበደሩት 270 ቢሊዮን ብር 70 በመቶ ለግል ዘርፉ የተሰጠ ነው
ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 19, 2020)፦ በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሚባለውን የአንድ ትሪሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ባንኮች ማሰባሰባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እድገት የቀጠለ መኾኑንና በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል።
ይህም በባንክ ዘርፍ ከፍተኛ የተቀማጭ ገንዘብ የተሰበሰበበት ዓመት መኾኑን ያመላከተ ነው ብለዋል። ለተቀማጭ ገንዘቡ መጠን እድገት፤ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን እንዲያሰፉ መደረጉ የባንክ ሒሳብ የከፈቱ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ጭምር ነው።
ይህም በመኾኑ የባንኮች ቅርንጫፎች 18 በመቶ ማደጉን፤ እንዲሁም ሒሳብ የከፈቱ ሰዎች ቁጥር ከ38.7 ሚሊዮን ወደ 50.7 ሚሊዮን ማደግ መቻሉን በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ አስረድተዋል። የፋይናንስ ዘርፉ በጥቅል 10.2 በመቶ እድገት የተመዘገበበት ዓመት ነውም ብለዋል።
የአገሪቱ ባንኮች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኮቹ የሰጡት የብድር መጠን 270 ቢሊዮን ብር እንደነበር በማስታወስ፤ ከዚህ ብድር ውስጥ 70 በመቶ የሚኾነውን ወይም 179 ቢሊዮን ብሩ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ በመኾኑ፤ ከዚህ ቀደም የባንኮች ከፍተኛ ብድር ለመንግሥት ይሰጣል የሚለውን አመለካከት የሚለውጥ ስለመኾኑም በዚሁ ማብራሪያ ላይ አመልክተዋል። (ኢዛ)