ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የፌዴራልና የትግራይ ክልል ፍጥጫ አሳስቦታል
ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ
ፍጥጫውን ትተው ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቋል
ኢዛ (ዓርብ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 30, 2020)፦ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከገቡበት ፍጥጫ ወጥተው ወደ ድርድር ይመለሱ ዘንድ ጠየቀ።
የአገራትን የፖለቲካ ሁኔታ በመከታተል፣ የግጭት ሥጋቶችን በማሳወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ፤ ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል የበለጠ የተካረረው፤ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሕገወጥ የተባለውን ክልላዊ ምርጫ ካካሔደ በኋላ ስለመኾኑ ጠቅሷል፡፤
ከዚህ ሕገወጥ ምርጫ በኋላ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በፌዴራል መንግሥቱ የተወሰዱትን እርምጃዎች ያተተው የግሩፑ ሪፖርት፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ፍጥጫ ወደ ንግግርና ውይይት መመለስ እንዳለበት አሳስቧል።
የግሩፑ ሪፖርት ጨምሮ እንዳመለከተው የፌዴራል መንግሥት የድጎማ በጀት ክልከላውን ለተወሰነ ጊዜ ሳይተገብር እንዲቆይ ወይም እንዲያዘገይ ጠይቋል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም የድርድር እንቅፋት ከሚኾኑ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ወጥቶ ለድርድር እንዲኾን አሳስቧል።
የፌዴራል መንግሥት ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ይኖርበታል የሚለው የግሩፑ ማሳሰቢያ፤ የፌዴራል መንግሥቱ ትዕግሥት ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።
ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በኩል ከክልሉ የሚወጡ የጦርነት ንግርቶችን ከማራገብ መቆጠብ እንዳለበትም ግሩፑ ጠቅሷል። (ኢዛ)



