የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ሲያከናውን (ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም.)

ቦርዱ ሰባት አባላት አሉት

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 5, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው በመደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማጽደቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን ሰየመ።

ለዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ሰባት አባላት ሲሆኑ፤ አባላቱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከሕግ ባለሙያዎች የተውጣጡ መኾናቸውም ተገልጿል።

በዛሬው የምክር ቤት ውሎ የቦርድ አባላት ኾነው የተሰየሙት አቶ ለማ ተሰማ የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፈ ምክትል ሰብሳቢ በመኾን እንዲያገለግሉ ነው። ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት ወይዘሮ ሀዋ ዓሊ፣ አቶ አለባቸው ላቀው፣ አቶ ዘሪሁን ጴጥሮስ፣ ወይዘሮ አስካለ ጥላሁን፣ አቶ ወንድሙ ግዛው ናቸው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላቱን በስድስት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምፅ የጸደቀ ሲሆን፣ የመርማሪ ቦርዱ ሥልጣን እና ተግባር ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦችን ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግ እና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢ-ሰብዓዊ እንዳይኾኑ መቆጣጠር እና መከታተል፣ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊ መኾኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ መስጠት የሚል ይገኝበታል።

ከዚህም ሌላ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙት ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ የሚሉ ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ