Fikreselassie Wogderess and Genet Ayele

በደርግ አገዛዝ ዘመን ከከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የነበሩት ጓድ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ (በግራ) እና ጋዜጠኛና ጸሐፊ ገነት አየለ አንበሴ (በቀኝ)፤ (ፎቶ ከገነት አየለ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተወሰደ)

"ምን ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ጠላቶች መጨረሻ ዓየን አይደል እንዴ?” ጓድ ፍቅረሥላሴ በመጨረሻ ሰዓታቸው የተናገሩት

ኢዛ (ቅዳሜ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 12, 2020)፦ በደርግ የአገዛዝ ዘመን ለዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት ጓድ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ማረፋቸው ተሰማ።

በደርግ አገዛዝ ዘመን ከከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የነበሩት ጓድ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ከደርግ ውድቀት በኋላ ከሌሎች የቀድሞ ባለሥልጣናት ጋር በእስር ቆይተው መፈታታቸው ይታወሳል።

ከእስር ከተፈቱ በኋላ “እኛና አብዮቱ” በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ የዛሬ ሰባት ዓመት (ታኅሣሥ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.) በፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ታትሞ ለገበያ እንደሚያበቃ መደረጉ አይዘነጋም።

ጋዜጠኛና ጸሐፊ ገነት አየለ አንበሴ በዛሬው ዕለት “እኔና ጓድ ፍቅረሥላሴ” እና “ኮለኔል መንግሥቱ በስልክ ከነገሩኝ” በሚሉ ርዕሶች በማኅበራዊ ትስስር ገጽዋ ስለ ጓድ ፍቅረሥላሴ ሁለት ጽሑፎች አስነብባለች።

“ኮሎኔል መንግሥቱ በስልክ ከነገሩኝ” በሚለው ጽሑፍ ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ "ጓድ ፍቅረሥላሴ እጅግ ከማምናቸውና ከምመካባቸው ጓዶቼ አንዱ ነበር። ሞቱን መቀበል አቃተኝ። የታሪክ አጋጣሚ እስኪለየን ከጎኔ ያልተለየ ቅን ጓዴ ነበር። በአብዮቱ ትግል ውስጥ አልፎ በጥረቱ ከደረሰበት ከፍተኛ ቦታ የደረሰ ሰው ነው። እንደብዙዎቻችን መላ ሕይወቱን ለአብዮቱና ለሕዝቡ የሰጠ፤ በግሉ ምንም ሀብት ወይም ንብረት ያልነበረው ሰው ነበረ" ማለታቸውን ጋዜጠኛና ጸሐፊ ገነት አስፍራለች።

“እኔና ጓድ ፍቅረሥላሴ” በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ትስስር ገጽዋ ስለ ጓድ ፍቅረሥላሴ የሚከተለውን አስነብባለች።

ሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ አላውቃቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋቸው እስረኛ ኾነው ነው። ኮሎኔል መንግሥቱን ዚምባብዌ ሔጄ ካገኘኋቸው በኋላ፤ አብረዋቸው የነበሩትን ጓዶቻቸውን ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ፈቃደኛ ኾነው ካነጋገሩኝ የደርግ አባላት አንዱ እሳቸው ነበሩ። በጥያቄያቸው መሠረት ስማቸውን ሳልጠቅስ ጓድ “ቁጥር …" በማለት መለያ ሰጥቼ ምስክርነታቸውን ለታሪክ እንዲቀር አድርገዋል። በዚህም እሳቸውንና ጓዶቻቸውን አመሰግናቸዋለሁ።

"ምን ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ጠላቶች መጨረሻ ዓየን አይደል እንዴ?" አሉኝ በፈገግታ። ይቺን ይዤያለሁ። - ነፍስዎን ይማርልን ጓድ ፍቅረሥላሴ። ገነት አየለ አንበሴ

ከዚያ በኋላ ከእስር ተፈትተው ሰላማዊ ኑሯቸውን ሲመሩ አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር። ባገኘኋቸው ቁጥር ረጋ ያለ ባሕሪያቸው፣ ትሕትናቸውንና ቅንነታቸውን ለማየት ችያለሁ።

በተፈጥሮ ካላቸው ቁጥብነታቸው ጋር ብዙ ማውራት ባይፈልጉም ብዙ የሚያውቁ መኾናቸውን ተረድቻለሁ። ከሁሉ በላይ ግን ልቤን የነካውን ነገር ላካፍላችሁ።

ከአንድ ወር ተኩል በፊት በትንሽ ነገር የተቀያየሙ ጓደኛሞች መኖራቸውን ሰማሁና በኔ አቅም ደፍሬ ሰዎቹን ለማስታረቅ መሞከር ፈራሁ። ካላቸው ተቀባይነት አንፃር ጓድ ፍቅረሥላሴ እንደሚረዱኝ ብተማመንም ትንሽ የጤና ችግር እንዳለባቸው ስለማውቅ ላስቸግራቸው አልፈለግሁም።

እሳቸው ግን ያለ አንዳች ማመንታት በቀናነት የማስታረቁን ሒደት እንደሚመሩ ፈቃደኛ መኾናቸውን ገልጸው እቤቴ መጡ። እያመማቸው በተከታታይ ሽምግልናውን ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ኾነው ነገሩን አሳክተው ተመራርቀን ተለያየን።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆስፒታል መግባታቸውን ስሰማ፤ ታመው እንዳስቸገርኳቸው እሳቸው ግን ለመልካሙ ሥራ ስቃያቸውን ችለው ፈገግታ ሳይለያቸው በመካከላችን እንደተገኙ ሳውቅ አዘንኩ። ደግነታቸውን አደነቅሁ።

የኔ ነገር መጠየቅ እወድ የለ? ጠጋ ብዬ ስለወቅታዊው ሁኔታ ጠያየቅኋቸው። የሚሰማቸውን እየነገሩኝ ትንሽ ቆየንና እንዴት ነው አሁን ተሽሎዎታል አደል? አልኳቸው።

"ምን ከእንግዲህ ወዲያ የኢትዮጵያን ጠላቶች መጨረሻ ዓየን አይደል እንዴ?" አሉኝ በፈገግታ። ይቺን ይዤያለሁ። - ነፍስዎን ይማርልን ጓድ ፍቅረሥላሴ። (ገነት አየለ አንበሴ)

ጋዜጠኛና ጸሐፊ ገነት አየለ አንበሴ ካሳተመቻቸው መጻሕፍት በግንባር ቀደምትነት የሚታወቀውና በብዛት የተነበበው “የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” የተሰኘው መጽሐፍ እንደኾነ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለጓድ ፍቅረሥላሴ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አክባሪዎች መጽናናትን ይመኛል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!