Jawar Mohammed (L), Bekele Gerba (R)

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ)

ፍርድ ቤት አንቀርብም ካሉ በፖሊስ ተገደው ይቅረቡ ተብሏል

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 17, 2020)፦ ለደኅንነታችን እንሰጋለን በሚል በእስር ከሚገኙበት ማረሚያ ቤት በቅርብ በሚገኝ ችሎት ጉዳያችን ይታይ የሚል አቤቱታ ያቀረቡትን የእነጃዋር መሐመድን አቤቱታ የተመለከተው ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

በእነአቶ ጃዋር መሐመድ በጽሑፍ ያቀረቡለትን አቤቱታ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የሕገ መንግሥት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር አቤቱታን ተመልክቶ ውሳኔ ያሳለፈው በዛሬው (ሐሙስ ታኅሣሥ 8 ቀን 2013 ዓ.ም.) ችሎት ነው።

ፍርድ ቤቱ የቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ጉዳያቸው በዚሁ ችሎት መታየቱን እንዲቀጥል ትእዛዝ ሰጥቷል።

በዚህ ችሎት በእነአቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ 24 ተጠርጣሪዎች የተካተቱ ሲሆን፤ ችሎቱ በአቅራቢያችን ይሁንልን ብለው አቤቱታ ያቀረቡት ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሃምዛ አድናን እና ሸምሰዲን ጠሃ ሲሆኑ፤ እነዚህ አራቱ አቤቱታ አቅራቢዎች በዛሬው ችሎት ያልተገኙ መኾኑ ታውቋል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት አቤቱታውን ውድቅ ከማድረጉም ሌላ፤ በተለዋጭ ቀጠሮ እነአቶ ጃዋር ፍርድ ቤት አንቀርብም ካሉ በፖሊስ ተገደው እንዲቀርቡ በማለት ለጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እነአቶ ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ሥር የዋሉትና የተከሰሱት በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240 በመተላለፍ፤ ብሔር እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት ቀስቅሰዋል የሚል የሚገኝበት ሲሆን፤ በሌሎች የሽብር ወንጀሎችም መከሰሳቸው ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!