አዲሶቹ የብር ኖቶች

አዲሶቹ የብር ኖቶች

ለቅያሬው የ14 ቀን ጊዜ ተሰጥቷል
ከ100 ሺሕ ብር በላይ ይዞ መቀየር አይቻልም

ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 30, 2020)፦ ትናንት በመቀሌ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው ከ100 ሺህ ብር በታች የአሮጌ ብር ኖቶች ቅያሬ መጀመሩ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ እንዳስታወቀው በትግራይ በተካሔደው የሕግ ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ተቋርጦ የነበረው የብር ኖት ቅያሬው በተወሰኑ የክልሉ ከተሞች ባንኮች ሥራ ጀምረው የብር ኖት ቅያሬውን እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው።

ባንኩ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በተወሰኑ ከተሞች የመብራትና የኢንተርኔት አገልግሎት የተጀመረ በመኾኑ፤ ባንኮች ተቋርጦ የነበረውን የብር ኖት ቅያሬ ሥራ ከሚጀምሩበት ቀን ጀምሮ በ14 ቀን ውስጥ አሮጌ የብር ኖቶችን እንዲቀይሩ ወስኗል።

የተሰጠው የ14 ቀን ጊዜ፤ ቅዳሜና እሁድን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ይህ የብር ኖት ቅያሬ ከ100 ሺህ ብር በታች ለሚቀይሩ ብቻ ተፈጻሚ የሚኾን ሲሆን፤ ከመቶ ሺህ ብር በላይ ያላቸው ግን በትግራይ የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት የተሰጠው ጊዜ በመጠናቀቁ፤ ከ100 ሺህ ብር በላይ ይዞ መቀየር የማይቻል ስለመኾኑ ባንኩ ካወጣው መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል። ይህንን ለማስፈጸምም ራሱን የቻለ ግብረኃይል ተቋቁሟል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ዘግተው ካቆሙ ከሁለት ወሮች በላይ ሲሆን፤ አሁንም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጭ ሌሎቹ የግል ባንኮች ሥራ አልጀመሩም።

ዛሬ በወጣው የብሔራዊ ባንክ መግለጫ መሠረት፤ ኢንተርኔትና መብራት ያሉባቸው አካባቢዎች የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት እንዲጀምሩ የሚያመላክት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!