ንግድ ባንክና ዳሽን ባንክ ከአፍሪካ 100 ምርጥ ባንኮች ውስጥ ገብተዋል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፳፬-24 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 4, 2008)፦ ሁለት የኢትዮጵያ ባንኮች ባላቸው ካፒታል ከአፍሪካ 100 ምርጥ ባንኮች ዝርዝር ውስጥ መግባታቸውን አፍሪካን ቢዝነስ መድሔት ዘገበ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 57ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ዳሽን ባንክ 88ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
እንደመድሔቱ መረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ57ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው፣ እስከ ሰኔ 2006 ባለው የ173 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካፒታልና የ4.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት ነው። በአትራፊነቱም ከዋነኛ አትራፊ ባንኮች ተርታ ሲሰለፍ፣ 90 ሚሊየን ዶላር ትረፍ ማስመዝገቡም ተገልጿል።
88ኛ የወጣው ዳሽን ባንክ ደግሞ እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም. ድረስ 60 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል እንዳለው፣ አጠቃላይ ሀብቱ 665 ሚሊየን ዶላር እንደሆነና ዓመታዊ ትርፉም 21 ሚሊየን ዶላር መድረሱን መጽሔቱ አስታውቋል።
እንደዘገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመላው ሀገሪቱ 205 ቅርንጫፎችና 2 ሚሊዮን ያህል ደንበኞች ሲኖሩት፣ በተቀማጭ ድርሻ 63.5 በመቶ ያህሉን ይይዛል። ዳሽን ባንክ በበኩሉ ከምሥራቅ አፍሪካ 23 ባንኮች የካፒታል መጠኑን ከ28 ሚሊዮን ዶላር ወደ 60 ሚሊዮን ዶላር በማሣደግ ከ23ኛ ደረጃ ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ማለቱም ተጠቅሷል።
በንዑስ ክፍለ አህጉራዊ ደረጃም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ4ኛ ደረጃ ሲቀመጥ የሞሪሽየስ ንግድ ባንክ፣ የኬንያው ባርክሌይስ ባንክና የሞሪታንያ ብሔራዊ ባንክ ከአንድ እስከ 3ኛ ደረጃ ያለውን ይዘዋል።
ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በባንክ ኢንዱስትሪው ቀዳሚ መሆናቸው ሲዘገብ፣ ከ100ዎቹ የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች 19ኙ የናይጀሪያ፣ 11ዱ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ መሆናቸው ታውቋል።
ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪካ ባንኮች (ስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ፣ ፈርስት ራንድ ባንኪንግ ግሩፕ፣ ኤ.ቢ.ኤስ.ኤ. ግሩፕ፣ ኒድ ባንክ፣ ኢንቨስቴክ ባንክ ሊሚትድ) ከአንድ እስከ 5ኛ ደረጃ ያለውን በመያዝ የመሪነቱን መንበር ተቆናጠዋል።