የአራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የወንጀል ምርመራ ተቋረጠ
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ
ከእስር የተለቀቁት የወንጀል ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ በመኾኑ ነው
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 17, 2021)፦ በሰሜን ዕዝ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ላይ ተሳትፈዋል ተብለውና በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙ አራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ ሲያካሒድ የነበረው የወንጀል ምርመራ ማቋረጡን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ።
ምርመራቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ የተወሰነላቸው የጦር መኮንኖች፤ ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ኢሻ ዘይኑ ትኩእ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ በርሄ ይልማ፣ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ገብረሚካኤል እና ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ መሸሻ መኾናቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ዛሬ አስታውቋል። እነዚህ የጦር መኮንኖች በሰሜን ዕዝ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው ተጠርጥረው፤ በመከላከያ ሠራዊት ክትትል ተይዘው ለምርመራ ቡድኑ ተላልፈው የተሰጡ እንደነበሩ ታውቋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ፤ ተጠርጣሪዎቹ ፈጸሙ በተባሉበት ወንጀል ምርመራ ሲካሔድባቸው የቆየ ቢኾንም፤ የምርመራ ቡድኑ ባደረገው ማጣራት፤ የወንጀል ተሳትፎአቸው ዝቅተኛ መኾኑን በመገንዘብ ምርመራው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑን ጨምሮ ገልጿል። (ኢዛ)



