የፀሐይ ባንክ ምሥረታ እየተካሔደ ነው
የፀሐይ ባንክ ምሥረታ በሼራተን አዲስ
ከ730 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ይዟል
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 18, 2021)፦ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሚኾነው ፀሐይ ባንክ፤ ይፋዊ ምሥረታ በሼራተን አዲስ እያካሔደ ነው።
ባንኩ ከ730 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እና ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ ካፒታል በመያዝ የሚመሠረት ነው። በአሁኑ ወቅት ፀሐይ ባንክን ጨምሮ ወደ 20 የሚኾኑ አዳዲስ ባንኮች ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ባንኩ ከአራት መቶ የማይበልጡ ባለአክሲዮኖች እንዳሉት ታውቋል።
እስከዛሬ የተመሠረቱት ባንኮች ዝቅተኛ የአክስዮን ሽያጭ 50 ሺህ ብር የነበረ ሲሆን፤ የፀሐይ ባንክ ዝቅተኛው የአክስዮን ሽያጭ ዋጋውን ከፍ በማድረግ 100 ሺህ ብር መኾኑን ለመረዳት ችለናል። አንድ ባለአክሲዮን መግዛት የሚችለው ከፍተኛው የአክሲዮን ዋጋ 100 ሚሊዮን ብር ነው።
ባንኩ የቦርድ አባላትን ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንደሚመርጥ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የአደራጅ ኮሚቴው ቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞው የሕብረት ባንክ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ናቸው።

ፀሐይ ባንክ የፀሐይ ኢንሹራንስ እኅት ድርጅት እንደኾነ ታውቋል። በኢትዮጵያ የባንኮችና ኢንሹራንሶች ታሪክ፤ በመጀመሪያ ኢንሹራንስ ድርጅት አቋቁሞ ወደ ባንክ ምሥረታ በመሸጋገር፤ ከሕብረት ኢንሹራንስ ቀጥሎ ፀሐይ ኢንሹራንስ ሁለተኛው ኾኗል። ፀሐይ ኢንሹራንስ ከተመሠረተ ዘጠነኛ ዓመቱን በሚቀጥለው ወር ይይዛል። (ኢዛ)



