የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ጋዜጣዊ መግለጫ

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም.

የትርፍ ሕዳጋችን ከፍ ማለት አለበት ብለዋል
የዱቤ ሽያጭ እንዲቀር መወሰኑ ችግር ይፈጥራል በሚል ሰግተዋል

ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 20, 2021)፦ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር የሚታሰብላቸው የትርፍ ሕዳግ አነስተኛ በመኾኑ የትርፍ ሕዳግ መጠኑን እንዲስተካከልላቸው ጠየቁ።

የማኅበሩ አመራሮች በሰጡት መግለጫ፤ የነዳጅ አዳዮች በአንድ ሌትር እየታሰበላቸው ያለው የ23 ሳንቲም ሕዳግ በቂ ካለመኾኑም በላይ፤ አትራፊ ኾነው ሥራቸውን ለመቀጠል እንዲያስችላቸው የትርፍ ሕዳግ መጠኑን መንግሥት ያሳድግላቸው ዘንድ የጠየቁ ሲሆን፤ የትርፍ ሕዳግ መጠኑም እስከ 80 ሳንቲም ድረስ መኾን ይገባዋል ብለዋል።

ማኅበሩ የጠየቀው የትርፍ ሕዳግ መጠን ከሦስት እጥፍ በላይ እንደኾነ ያሳያል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሦስት ሳንቲም የትርፍ ሕዳግ መሥራታቸውን የሚገልጹት የማኅበሩ አመራሮች፤ አሁን 23 ሳንቲም የደረሰላቸው በብዙ ሙግትና ልመና መኾኑንም ገልጸዋል።

በ23 ሳንቲም የትርፍ ሕዳግ መሥራታቸው ኪሣራ ውስጥ ጭምር እየከተታቸው መኾኑ ሳያንስ፤ እንደገና ከነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ ወስደው ሲሸጡ የነበረውን ነዳጅ፤ አሁን እጅ በእጅ ክፍያ እንዲረከቡ እያሳወቁዋቸው በመኾኑ፤ ሌላ ችግር ውስጥ ልንገባ ነው በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት እስካሁን ለነዳጅ ኩባንያዎች ነዳጅ ሲያቀርብ የነበረው በዱቤ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ በተሰጠ ውሳኔ መሠረት ነዳጅ በዱቤ እንደማያቀርብ አሳውቋል።

ይህም ውሳኔ ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተገበር እንደሚኾን የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚሁ ውሳኔ መሠረትም የነዳጅ ኩባንያዎች ለነዳጅ አዳዮች እያስተላለፉ ባሉት መልእክት እነርሱም የዱቤ ሽያጭ እንደሚያከናውኑ በማስተወቃቸው የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ላይ ሥጋት ፈጥሯል።

የማኅበሩ ሥጋት ነዳጁ በዱቤ የማይሰጣቸው ከኾነ ቀድሞ ከፍሎ ለመረከብ አቅም ስለማይኖራቸው፤ የነዳጅ ሥርጭቱ ላይ ችግር ይፈጥራል በማለት መንግሥት ይህንን ውሳኔ መልሶ እንዲመለከተው ጠይቀዋል።

እስከዚያም የመተግበሪያ ጊዜውን እንዲያራዝም የጠየቁት የማኅበሩ አመራሮች፤ በዚህ ውሳኔ ዙሪያ ያገባናል በማለት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ለመንግሥት አካላት ያቀረቡት ጥያቄ አወንታዊ መልስ ባለማግኘቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

አሁንም ጉዳዩ አሳሳቢና በነደጅ ሥርጭቱ ላይ ችግር ስለሚፈጥር፤ መንግሥት በአስቸኳይ ያነጋግረን በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በትናንቱ (ዓርብ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም.) ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በአሁኑ ወቅት 35 የነዳጅ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ኩባንያዎች ከ800 በላይ የነዳጅ ማዲያዎች አላቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ