የትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይል በጄኔራል ዮሐንስ እንዲመራ ተወሰነ
ጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል
ጄኔራሉ የሕወሓት አባል እና በመከላከያ ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ናቸው
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 3, 2021)፦ የትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይል በጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል አመራር እየታገዘ የመልሶ ግንባታና የማረጋጋት ሥራው እንዲቀጥል መወሰኑ ተገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል የተከናወኑ ሥራዎችንና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ከክልሉ ከአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይልና ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ከተወያዩ በኋላ ከዛሬ የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረኃይሉ በጄኔራል ዮሐንስ ገብረመስቀል አመራር እየታገዘ ሥራውን ይቀጥላል ሲሉ ዶ/ር ዐቢይ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
ጄኔራል ዮሐንስ የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ባደረሰ ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ካደረጉዋቸው ሦስት ጄኔራሎች መካከል አንዱ ናቸው።
ጄኔራል ዮሐንስ የሕወሓት አባል እና በመከላከያ ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን፤ ከሠራዊቱ ተገልለው የቆዩ ናቸው። የሕወሓትን ቡድን በመቃወም እና አሠራሩን በመንቀፍ የሚታወቁ ናቸው። (ኢዛ)



