የመጋቢት 4 ግጥምጥሞሽና አሳሳቢው ኮቪድ 19
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኮሮና ክትባት ሲወስዱ
በቫይረሱ የተጠቃው የመጀመሪያው ሰው በተገኘ ልክ በዓመቱ፤ ክትባቱም መሰጠት ተጀመረ
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 13, 2021)፦ ዛሬ መጋቢት 4 ቀን ነው። ልክ የዛሬ ዓመት በወቅቱ አስደንጋጭ የሚባል ዜና የተሰማበት ዕለት ነው። ይህም ዓለምን ሲንጥ በቆየው የኮቪድ 19 ቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያው ሰው መገኘቱ ይፋ የደተረገበት ነው። የጤና ሚኒስቴር ኾነው በተሾሙ በቀናው ልዩነት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በቴሌቭዥን ብቅ ብለው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በቫይረሱ የተጠቃ አንድ ሰው መገኘቱን የነገሩን ዶክተር ሊያ ታደሰ ነበሩ።
በዚህ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ ሪፖርት ያደረገችበት ይህ ቀን ዛሬ አንደኛ ዓመቱን ይዟል። ይህ ሪፖርት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ወራት ሰዎች ከቫይረሱ ለመጠበቅ በብርቱ ሲጥሩ ነበር። ቆይቶ ይህ ጥንቃቄ እየላላ መጥቶ ዛሬ ላይ ደርሷል።
በየዕለቱ በቫይረሱ የተያዙ፣ የሞቱ፣ ያገገሙ፣ … እየተባለ ሪፖርት መደረጉ ቀጠለ። የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ በተገኘበትና በዓመቱ በዛሬው ዕለት ብቻ የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 7,654 ግለሰቦች ውስጥ 1,483 ቫይረሱ ሲገኝባቸው፤ 30 ሰዎች ሞተዋል።
ዛሬ ልክ በአንድ ዓመቱ በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ጠቅላላ ቁጥር 174,054 ሲደርስ፣ የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ 2,221,834 እንደኾነ ታውቋል። በቫይረሱ ተይዘው የሞቱ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 2,540 መድረሱን ለማወቅ ተችሏል። ከበሽታው ያገገሙት ደግሞ 142,041 መኾናቸውንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
አሁን ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ኾኗል። መካከል ላይ ቀንሶ የነበረው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ካለፉት ሁለት ሦስት ወራት ወዲህ እንደገና እየጨመረ መጥቷል።
በትናንትናው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሠረት በ24 ሰዓታት ውስጥ የላብራቶሪ ምርመራ ካደረጉ ሰዎች ውስጥ 1,361 በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በ24 ሰዓት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት ኾኗል ቢልም፤ የዛሬው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 1,483 መድረሱ፤ እስካሁን ከፍተኛው ቁጥር ለመኾን በቅቷል። ቀስ በቀስ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የተጠቂዎች ቁጥር ብቻ ሳይኾን በቫይረሱ ተይዘው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በመጨመሩ በ24 ሰዓት ውስጥ ትናንት 27 የሞቱ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ የሟቾች ቁጥር 30 መድረሱ ሪፖርት ተደርጓል።
ይህም የቫይረሱ ሥርጭት አሁንም እየጨመረ መምጣቱንና አሳሳቢ ከሚባል ደረጃ ላይ መድረሱ ነው። በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፤ የቫይረሱ ሥርጭት ከፍ እያለ መምጣቱን የሕክምና መስጫ ተቋማትም መጨናነቅ የሚታይባቸው መኾኑን ነው።
ሁኔታው የዜጐች ጥንቃቄ ካልታከለበት የበለጠ አሳሳቢ እንደሚኾን ታምኗል። በአንድ ዓመት ውስጥ ከ2,540 በላይ ዜጐችን በዚህ በሽታ አጥተናል። ከ142,041 በላይ የሚኾኑ ዜጐች በቫይረሱ ተጠቅተዋል። ይህ መረጃ ጤና ሚኒስቴር የሚያውቀው ሲሆን፣ የላብራቶሪ ምርመራ ሳይደረግለት እና በዕለታዊ ሪፖርት ውስጥ ሳይካተት በቫይረሱ የሚያዘውና የሚሞተው ሰው ቁጥር ቢካተት ችግሩ ከዚህም በላይ ይኾናል። ይህም አሁንም ጥንቃቄ የሚያሻው ሕብረተሰቡም ችግሩን በመገንዘብ እሱንና ሌሎችን መጠበቅ ይኖርበታል።
ከአንድ ዓመት ጉዟችን የተገነዘብነው በሽታው መልሶ ብዙዎችን እያጠቃ መኾኑን ነው። በአንጻሩ ግን መጋቢት አራትን እንደ ገና የምናስታውስበት ሌላ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይህም ኢትዮጵያ ከአንድ የውጭ ተቋም ያገኘችውን 2.2 ሚሊዮን ክትባት ተረክባ፤ ክትባቱን ያስጀመረችበት ዕለት ዛሬ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ኾኗል።
ክትባቱ መጀመሩ አንድ ተስፋ ቢሆንም፤ ቫይረሱ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ ዋነኛ መድሃኒቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። አዎ ጥንቃቄ!! (ኢዛ)



