ተኩስ አሁንም አለ

አቶ ሲሳይ ዳምጤ፣ የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ
ታጣቂ ቡድኑ ከአጣየ ውጭ ጥቃቱን ለማስፋት እየሞከረ ነው ተባለ
ሕዝቡ ነገሮችን በትእግሥት እንዲመለከት ተጠየቀ
ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 21, 2021)፦ በአጣየና በአካባቢው በተደራጀ ሁኔታ ጥቃት ያደረሰው የታጠቀ ኃይል አሁንም ተኩስ መግጠሙንና ጥቃቱን ወደ ማጀቴ፣ ሰንበቴና ሸዋ ሮቢት አካባቢዎች ለማስፋት እየሞከረ መኾኑን የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የተደራጀ ያሉት ኃይል የቡድን መሣሪያ ጭምር ታጥቆ ጥቃት ማድረሱን እና በዚህም ሰዎች መሞታቸውን፣ መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም ሀብትና ንብረት መውደሙንም አረጋግጠዋል።
የመንግሥት ተቋማት ጭምር ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት ኃላፊው፤ ድርጊቱ የፖለቲካ መዋቅሩን፣ የፖለቲካ መሪዎችን እና ሕዝብን ያሳዘነ ነው ብለዋል።
ጥቃቱን በአካባቢው የጸጥታ አካላት ለመመከት ጥረት ስለመደረጉ ያስታወሱት አቶ ሲሳይ፤ ነገር ግን ጥቃቱ በቡድን መሣሪያ የታገዘ በመኾኑ ባለው ኃይል ብቻ መመከት እንዳልተቻለ አመልክተዋል።
አሁን ተጨማሪ ልዩ ኃይል ሚሊሻ እና የፌዴራል ፖሊስ መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. መግባቱንና አጣየ እና አካባቢውን ለማረጋገጥ ተሞክሯል። ኾኖም የታጣቂው ኃይል አሁንም ድረስ ተኩስ እየገጠመ ሲሆን፣ ጥቃቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየሞከረ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የክልሉ የጸጥታ መዋቅርም ወደ አካባቢው በመሔድ ከሰሜን ሸዋ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እየሠራ ነው ብለዋል።
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በስሜት ሳይኾን በሰከነ መልኩ ወቅቱን መሻገር እንዳለበት ያሳሰቡት ኃላፊው፤ ሆደ ሰፊ እንሁን ስንል የአማራ ሕዝብን አሳልፈን እንስጥ ማለት አይደለም በማለት አክለዋል።
አያይዘውም ሕዝቡ ትእግሥት በተሞላበት አግባብ ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ያደረጉት ኃላፊው፤ በሽብር ቡድኑ ላይ የሚካሔደውን የሕግ ማስከበር ሥራው ይጠናከራልም ብለዋል። (ኢዛ)