Shew Robit town

ሸዋ ሮቢት ከተማ

በሸዋ ሮቢት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘግተው ውለዋል

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 22, 2021)፦ ከሰሞኑ የሰው ሕይወት የቀጠፈው፣ ሀብት እና ንብረት ያወደመው የአጣየ እና የአጎራባች አካባቢዎች ጥቃትን ተከትሎ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር አሁንም ያለ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት የእንደ ሸዋ ሮቢት ያሉ ከተሞች የተለያዩ አገልግሎት ተቋማት ተዘግተው ውልውዋል።

የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክቶ የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ እንዳስታወቀው፤ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናቸው። ከአካባቢዎች ነዋሪዎች የሚገኙ መረጃዎች ግን፤ ችግሩ የተከሰተባቸው ቦታዎች አሁንም የጸጥታ ችግር እና ሥጋት ያለባቸው መኾኑን ያመላክታሉ።

ሰርገው የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በመኖራቸው ሥጋት እንዳለባቸው የሚጠቁሙት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በተለይ በሸዋ ሮቢት ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ኾነው ውለዋል። የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎችም የጸጥታ ሥጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ነገር ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሸዋ ሮቢት ከተማ በመገኘት ነዋሪዎችን በማረጋጋት ላይ ናቸው ብሏል። ይሁን እንጂ ሰርጎ ገቦች እና ተመሳስለው የሚኖሩ አካላት አሁንም የሕብረተሰቡ ሥጋት መኾናቸው አንስተዋል።

የአማራ ክልል መንግሥትም አካባቢውን በደንብ ማደራጀት እና ማኅበረሰቡ እራሱን እንዲከላከል ማድረግ እንዳለበትም ነዋሪዎች ይገለጹ ሲሆን፤ ጥቃት በሚያደርሱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድም የሕዝቡን ሰላም እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይል ቁጥጥር ሥር ስለመኾናቸው ይግልጻል። የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ሕብረተሰቡን ለማረጋጋት ቅድሚያ ሰጥተው እየሠሩ መኾኑን አመልክተዋል። አካባቢዎቹን የማረጋጋትና ወደ ነበሩበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሠራ መኾኑንም መምሪያው አስታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ