የዘር ማጥፋት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ

ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ በሚል በምትታወቅ ቀበሌ ውስጥ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት መፈጸሙን ተከትሎ በበይነመረብ የተሰራጨ ፎቶ

መንግሥት ድርጊቱን እንዲያስቆም አሳስበዋል
እጃቸው ያለበት ባለሥልጣናትም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል
“አፋቸውን የከፈቱ ጅቦች ትንንሽ አይጦችን በመላክ ኢትዮጵያን ለመዋጥ እየጣሩ ነው” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ

ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 4, 2021)፦ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃትን በመቃወም እና ድርጊቱ እንዲቆም የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ አቋማቸውን ያንጸባረቁበትን መግለጫ ትናንት አውጥተዋል።

እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በጋራ ኾነው ተመሳሳይ አቋማቸውን ያንጸባረቁት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ እናት ፓርቲ፣ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እና የኢትየጵያ ዜጐች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ናቸው።

ፓርቲዎቹ ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉት መግለጫቸው፤ ማንነትን መሠረት አድርጐ የሚፈጸም ጥቃት (ዘር ማጥፋት) እንዲቆም ከመጠየቃቸውም በላይ፤ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር አሳስበዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት ያወገዙት አምስቱ ፓርቲዎች፤ የፌዴራል መንግሥትም ኾነ የክልል መንግሥታት ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የፓርቲዎቹ በዚህ መግለጫቸው ላይ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በዚሁ ጥቃት ዙሪያ ገለልተኛ ኮምሽን በማቋቋምና ምርመራ በማድረግ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

እንዲህ ባሉ አገራዊ አደጋዎች ወቅት ፓርቲዎቹ በጋራ እንደሚሠሩም በዚሁ መግለጫቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ሌላው አፅንኦት ሰጥተው ሊፈጸም ይገባል ያሉት፤ በተለያዩ ጥቃቶች ላይ የሚሳተፉ ግለሰብና ቡድኖች እርምጃ እንዲወሰድ ነው። መንግሥት በጥቃቱ አድራሾች ላይ ብቻ ሳይኾን፤ በጥቃቱ የተሳተፉና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይም በፍጥነት ተጣርቶ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም መንግሥትን አሳስበዋል።

ከዚህም ባሻገር በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ዘር ተኮር ጥቃት ለማውገዝና ለማጋለጥ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ጥሪ ያስተላለፉት እነዚህ አምስት ፓርቲዎች፤ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ ያድርግም በማለት ይህ እንዲፈጸምም ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ሰሞኑን በተለይ በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው ዘር ተኮር ጥቃት ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የኾነ ሲሆን፤ ድርጊቱ ከየአቅጣጫው ተቃውሞ እያስነሳ ነው። ጥቃቱን ተከትሎ መንግሥት የጥቃቱ አድራሽ ናቸው ያላቸውን የማያዳግም እርምጃ እወስድባቸዋለሁ ብሎ የጸጥታ ኃይል ወደ አካባቢው በመላክ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው ተብሏል።

በትናንትናው ዕለትም በምዕራብ ወለጋ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን የማደን ሥራ ስለመጀመሩ ተነግሯል።

ሰሞናዊ ጥቃቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናውው ዕለት፤ በንጹሐን ዜጐች ላይ ጥቃት ለማድረስ፣ ኢትዮጵያን ለመበታተን በሚሠሩ ተላላኪ ሽፍቶች ላይ ባለፉት ሦስት ቀናት የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ገልጸዋል።

“አፋቸውን የከፈቱ ጅቦች ትንንሽ አይጦችን በመላክ ኢትዮጵያን ለመዋጥ እየጣሩ ነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ይህ እኩይ ዓላማ እንደማይሳካ ገልጸው፤ ሕግ በማስከበሩ ዙሪያ ዜጐች ከጸጥታ ኃይሉ ጋር እንዲቆም ጠይቀዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ