Yonatan Tesfaye

አቶ ዮናታን ተስፋዬ

አንዱ ተሿሚ ዮናታን ተስፋዬ ነው

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 5, 2021)፦ በቅርቡ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በለቀቁት በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ምትክ እና በሹመት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት በሔዱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ምትክ አዳዲስ ኃላፊዎች ተሾሙ።

በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሹመት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ መሐመድ እንድሪስ አሕመድ ናቸው።

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ባለሥልጣኑን በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ የተሾሙት ደግሞ አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና አቶ ግዛው ተስፋዬ ናቸው።

በእነዚህ ኃላፊነቶች የተሾሙት ሦስቱ የባለሥልጣኑ ዋና እና ምክትል ዳይሬክተሮች ከዛሬ ጀምሮ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።

ከዛሬው ተሿሚዎች ቀደም ብሎ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በፍቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ በማቅረብ የመንግሥትን ውሳኔ ሲጠባበቁ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ አዲስ ዋና ዳይሬክተር ሊሾም ችሏል።

የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ በኃላፊነት የቆዩት ከመጋቢት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር።

በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ከሁለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት የፌዴራል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ም/ዋና ዳይሬክተር ኾነው በመሾማቸው፤ የምክትል ዳይሬክተርነቱ ቦታ ክፍት ኾኖ ቆይቶ፤ በዛሬው ዕለት ሁለት አዳዲስ ዋና ዳይሬክተሮች ሊሾሙ ችለዋል።

በዛሬው ዕለት ከተሾሙት ውስጥ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከለውጡ በፊት የነበረውን ሕወሓት መራሽ አስተዳደር በመቃወም እና በመታገል ይታወቃል። በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ይታገሉ ከነበሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዚህም በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ