በዝግ ችሎት ይሰማ የተባለው ምስክርነት ውድቅ ኾነ
አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ)
በእነ አቶ ጃዋር ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸው ይሰማ ተብሎ ብይን ተሰጠ
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 6, 2021)፦ ዓቃቤ ሕግ በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ በዝግ ችሎት ላሰማ ያለው የምስክር የአሰማም ሒደት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፤ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ብይን ተሰጠ።
በምስክር ጥበቃ አዋጅ መሠረት ለምስክሮቼ ደኅንነት ሲባል ከመጋረጃ በስተጀርባ እና በዝግ ችሎት ምስክሮቼን ላሰማ ሲል ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን አቅርቦ የነበረው ባለፈው ቀጠሮ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም.) ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግ ጥያቄን ውድቅ አድርጓል።
እነ አቶ ጃዋር የዓቃቤ ሕግን በዝግ ችሎት ላሰማ የሚለውን ጥያቄ የመከላከል መብታችንን የሚገድብ ነው በማለት አቤት ብለው ነበር። ከዚህም ሌላ የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ታማኝነት የለውም በማለት የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ ማመልከታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥያቄውን መርምሮ ውድቅ ማድረጉ ታውቋል።
ችሎቱ በዛሬው ዕለት ተሰይሞ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በተገኙበት ጉዳያቸውን ተመልክቷል።
በዚህም ዓቃቤ ሕግ በምስክር ጥበቃ አዋጅ መሠረት ጥበቃ ተደርጓል ብሎ ከመጥቀስ በዘለለ ምስክሮች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በማስረጃ ያላስደገፈ በመኾኑ፤ በቂ ምክንያት ኾኖ አላገኘሁትም ሲል ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ብይን እንደሰጠ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ግን ተከሳሾቹ የምስክር ዝርዝር ይገለጽልን ብለው ያቀረቡት አቤቱታ ለምስክሮች ደኅንነትና መብት ጥበቃ ሲባል የምስክሮች ማንነት እንዳይገለጽ ሲል ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። (ኢዛ)



