የመራጮች የምዝገባ ጊዜ ሊራዘም ነው
ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልል መስተዳድሮች ጋር መክረዋል
ልዩነቶች በጥይት ሳይኾን በምርጫ ካርድ የሚፈቱበት ነው አሉ
ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 22, 2021)፦ በተጠበቀው ልክ አለመከናወኑ እየተገለጸ ያለው እና ከነገ በስቲያ የሚጠናቀቀው የመራጮች ምዝገባ ጊዜ እንዲራዘም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ጊዜውን እንደሚያራዝም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች የምዝገባ ጊዜ ብሎ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ እንደኾነ ይታወቃል።
እስካሁን እየተሰባሰቡ ካሉ መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው በጸጥታ ችግር ምዝገባ ካልተጀመረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሌላ በሌሎቹ ቦታዎች ምዝገባው ቢጀመርም የተጠበቀውን ያህል አልነበረም።
በዚህ ሳምንት ግን በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ካለፉት ሦስት ሳምንት ወዲህ በርካቶች የተመዘገቡበት ነው ተብሏል።
45 ቀናት የቀሩት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ (ምርጫ 2013) ሰላማዊ ነፃና ፍትሐዊ እንዲኾን መንግሥት ያለበትን ድርብ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከክልል መስተዳድሮች ጋር በዛሬው ዕለት በምርጫው ዙሪያ በመከሩበት ወቅት ነው።
የክልል የርዕሰ መስተዳድሮች በምርጫው ዙሪያ ስለተከናወኑ የእስካሁን ተግባራትን አቀረቡ በተባለው ሪፖርት በሲዳማ፣ በኦሮሚያ፣ በድሬዳዋና በአዲስ አበባ የመራጮች ምዝገባ ከ80 በመቶ በላይ መከናወኑን አመልክተዋል። በሌሎች ክልሎችም ቢኾን የመራጮች ምዝገባ 50 በመቶ ስለመከናወኑም ተገልጿል።
በዚህ መረጃ መሠረት አሁንም የመራጮች ምዝገባ በሚፈለገው ደረጃ ያለመከናወኑን የሚያመላክት ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት የክልል መስተዳድሮች በቀረበው ሪፖርት የመራጮች ቁጥርን በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት ነው።
ኾኖም ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልል ርእእሰ መስተዳድሮች ጋር በመከሩበት ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መገኘቱ ተጠቅሷል።
በዕለቱ በምርጫ ቦርድ በኩል የመራጮች ምዝገባ ሒደቱን በተመለከተ ሰጠ የተባለው መረጃ ባይኖርም፤ ፓርቲዎች የምዝገባው ጊዜ ይራዘም የሚል ጥያቄ መቅረቡን አመልክቷል።
በዚህም መሠረት ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን በመቀበል የምዝገባ ጊዜውን ሊያራዝም ወስኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በተደረገው ምክክር ላይ በመረጃ ገጻቸው የሚከተለውን ብለዋል።
“የ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ሒደት ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ እንዲኾን በቁርጠኝነት እየሠራን ነው። ባለፈው ከክልል አመራሮች እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባካሔድነው ስብሰባ፣ ቀሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ እና ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጣችን ይታወሳል። ዛሬ ቀጣይ ስብሰባ አካሒደን፣ ክንውኑን ገምግመናል። ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ልዩነቶች በጥይት ሳይኾን በምርጫ ካርድ አማካኝነት የሚፈቱበት ነው። በምርጫ ሒደት፣ ዜጎች የተማመኑበትን በሙሉ ልብ ለመምረጥ እና ዴሞክራሲያዊ ሒደትን ለመገንባት ንቁ ተሳትፎ የማድረግ እድል ያገኛሉ። መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያስፈነጥር እንደመኾኑ፣ በጋራ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ያስፈልገናል። ነገን እንዲወስኑ፣ ዛሬ ይመዝገቡ!” (ኢዛ)



