በ10 ቀናት ከ16 ሺህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ
ኮቪድ 19 (COVID-19): ኮሮና ቫይረስን በምስል ለማሳየት በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል (CDC) የተሠራጨ
የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ሩብ ሚሊዮን ደርሷል
በኮሮና በቀን 28 ሰዎች እየሞቱ ነው
ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 24, 2021)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) በእጅጉ እየተስፋፋ ስለመምጣቱ እየታየ ሲሆን፤ በተለይ ባለፉት አሥር ቀናት ብቻ 16 ሺህ 780 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው፣ 283 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ወረርሽኝ ሕይወታቸው አልፏል።
ዛሬ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት አሥር ቀናት 16 ሺህ 780 የሚኾኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙት፤ ለ74 ሺህ 338 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጐላቸው ነው።
ይህ አኀዝ በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ምን ያህል እያደገ መምጣቱን ሲሆን፤ በአሥር ቀናት ውስጥ የሟቾች ቁጥር 283 መኾኑም በቫይረሱ ተጠቅተው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሔዱንና በቀን በአማካይ እየሞተ ያለው ሰው 28 መኾኑን ያሳየ ኾኗል።
እስከ ትናንት ድረስ እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ወደ ሩብ ሚሊዮን መድረሱ ታውቋል።
ዛሬ በወጣው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃም፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 249 ሺህ 292 መድረሱን ነው። እስካሁን በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 3 ሺህ 511 ደርሷል። በአጠቅላይ እስካሁን የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር 2.53 (ሁለት ነጥብ አምስት ሦስት) ሚሊዮን ነው። (ኢዛ)



