ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በሁለት ቢላዎች የሚበሉ የውስጥ ሰዎችን አጸዳለሁ አለ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ስብሰባውን ባካሔደበት ወቅት
መግለጫው በሁለት ቢላዋ የሚበሉት አካላትን በግልጽ አልጠቀሰም
ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 24, 2021)፦ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በየአቅጣጫው የምናየው የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ቤት እና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በአገር ውስጥ ብቻ የተመሠረተ ያለመኾኑን ገልጾ፤ በመጀመሪያ በውስጥ ያሉትን ባለሁለት ቢላዎች እንደሚያጸዳ አስታወቀ።
ብሔራዊ ምክር ቤቱ በወቅታዊ አገራዊና ቀጠናዊ የደኅንነት እና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፤ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ግጭቶች በአገር ውስጥ የተመሠረተ ያለመኾኑን በማመልከት፤ ችግሩን በማቀጣጠል ደግሞ በሁለት ቢላዎች የሚበሉ አካላት መኖራቸውን ጠቁሞ፤ እነዚህን ባለሁለት ቢላዎች እናጸዳለን በማለት ገልጿል።
በሁለት ቢላዎች የሚበሉ ያላቸውን ወገኖች፤ “ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በኢትዮጵያ የሚዶልቱ ናቸው” በማለት የጠቀሰው ይኸው መግለጫ፤ እነርሱ ከውጭ ጠላቶች በላይ ዋነኛ ጠላቶቻችን ናቸው በማለት፤ በውስጥ ኾነው ሲሸፍጡ የቆዩትን እንደሚያጸዳ አመላክቷል።
በሁለት ቢላዋ የሚበሉ ብሎ የመደባቸው ወገኖች የትኞቹ እንደኾኑ በስም በቀጥታ ጠርቶ ባያስቀምጥም፤ ከውጭ ጠላቶ ጋር የሚተባበሩ መኾናቸውን አስቀምጧል።
መግለጫው ይህንንም ሲያብራራ፤ አገሪቱ የሁሉም የጋር ቤት መኾኗን እና የሁሉም ቤቶች በዚህች ትልቅ ቤት ውስጥ ያሉ የቤቱ ክፍሎች መኾናቸውን በመግለጽ፤ “በየክፍሎቻችን ተወሽቀን ያለነው ሁላችንም የጋራ ቤታችንን አጽንተን በማቆየት ላይ ተመሳሳይ አቅምና አቋም የለንም። ቤትን ከውጭ የሚመጣ ኃይል ብቻውን አያፈርሰውም። የውስጦቹ ካልተባበሩት በቀር።” በማለት የብሔራዊ ድኅንነት ምክር ቤቱ በሰጠው መግለጫ አትቷል።
አገሪቱን በቤት በመመሰል የገለጸው ይኸው መግለጫ፤ “የቤቱ ሰዎች የውጭ አፍራሾች በሦስት መንገድ ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሊተባበሯቸው ይችላሉ። ኾን ብለው፣ ሞኝ ኾነው እና ተኝተው።” ሲል ሦስት ዐይነት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ለማስረዳት ሞክሯል።
“ዛሬ ታላቋ ቤታችን ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ናት። ሦስቱም ዐይነት ልጆች አሏት። ከውጭ ጠላቶቿ ጋር 1) ይሁነኝ ብለው በዓላማ ለማፍረስ የሚሠሩ፤ 2) በዓላማ ባይገጥሙም በውጤት ከውጭ አፍራሾች ጋር የሚሠሩ፤ 3) ቤታቸው ሲቃጠል እያዩ ከመንቃት ይልቅ በሙቀቱ ተከናንበው የተኙ።” በሚል ይኸው መግለጫ ያትታል።
እነዚህ በዚህ መልክ የተፈረጁትና በሁለት ቢላዋ ይበላሉ የተባሉት ወገኖች፤ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ ይኹኑ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ወይንም በጸጥታ ተቋማት ውስጥ ያሉ ይሁኑ መግለጫው በግልጽ አላስቀመጠም።
ምርጫ 2013 በአግባቡ ተካሒዶ እንዲጠናቀቅ እና ከዚህ በኋላ በምክር ቤቱ ይወሰዳሉ የተባሉ እርምጃዎችም በዚሁ መግለጫ ላይ ተካትተዋል። የምክር ቤቱ ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
በወቅታዊ አገራዊና ቀጠናዊ፣ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ የሰጠው መግለጫ
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፣
ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ለውጥ ጎዳና የገባነው በመንገዱ ላይ ችግሮች አይገጥሙንም በሚል እሳቤ አልነበረም። አገራችን ትከሻ ላይ የተቆለለውን የበዛ ችግር ከነውስብስብነቱ ተረድተን እንጂ፤ አቅልለን ዓይተን አልተነሳንም። ለዘመናት ሲከመር ቆይቶ ወደ ግዙፍ ተራራነት የተለወጠው አገራዊና ቀጠናዊ ችግሮች በቀላሉ መወገድ ቢችሉ ጥሩ ነበር።
ነገር ግን ችግሮቹ እንኳን እርስ በእርስ እየተጓተትን ቀርቶ፤ አንድ ኾነንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድምጥማጣቸው የሚጠፋ አይደለም። ይሔንን በሚገባ አውቀን እስከ መጨረሻው ሕቅታ ዋጋ ለመክፈል ቆርጠን ነው የተነሳነው።
አገራችን ያሉባት ችግሮች ምንም ያህል እንደ ምድር አሸዋ ቢበዙ ፈጽሞ ከዜጎቿ አቅም በላይ እንደማይኾኑ ጽኑ እምነት አለን። የሚፈቱትም ተነጣጥለን ሳይኾን በአንድነትና በትብብር እንደኾነ ገና ከጅምሩ አሳውቀናል።
በወቅቱ ያለ ብዙ ፈተና በአንዲት ጀንበር የተለወጠች አገር ትኖረናለች ብለው የጠበቁ ሰዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ለውጡ ከአንድ አቅጣጫ ይመጣልም ብለው እንደታዛቢ ዳር ቆመው የሚመለከቱ መኖራቸውም እንዲሁ።
ያኔ የለውጥ ጉዞ በጀመርንበት ወቅት ሁሉም ሰው ከፍ ባለ ሞራልና በፌስታ ተሞልቶ የነበረ ቢኾንም፣ ሁሉም በጀመረበት የመንፈስ ከፍታ እንደማያጠናቅቅ ግልጽ ነበር።
አገራችን ለዘመናት ስትናፍቀው የኖረችው የተስፋ አድማስ ላይ ደርሰን ሁላችንም የመንካት እድሉ ይገጥመናል ብሎ ማሰቡም ሞኝነት ነው። በየመንገዱ የሚገጥመንን እሾህና ጋሬጣ ሳያቆስለን፣ እባብና ጊንጡ ሳይነድፈን፣ ሀሩርና ቃጠሎው ሳይለበልበን የምናልማትን የበለጸገች አገር መገንባት ብንችልማ ኖሮ ገና ድሮ በአደረግነው ነበር።
በረሃውን ሳናቋርጥና ባሕሩን ሳንሻገር ጉዞው ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡ ሰዎች ከመጀመሪያውም ተሞኝተዋል።
ከፊታቸው የተዘረጋውን ፈተና ቀድመው ያላዩ፣ ጉዞው መኻል ላይ ወገባቸው ዝሎ መንቀጥቀጥ ሲጀምር ቢናደዱ፣ መበሳጨት ያለባቸው በሌላ አካል ሳይኾን በተሳሳተ ግምታቸው ነው።
አሁንም ቢኾን ይበልጥ ወደ ተስፋ ሰገነታችን እየቀረብን በመጣን ቁጥር ፈተናው እንደሚበረታ መረዳት ይኖርብናል።
በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ግጭቶች፣ የሰላም ማጣትና የደኅንነት ሥጋቶች በለውጥ ጉዞአችን በእጅጉ ከፈተኑን ፈተናዎች ጎራ የሚመደቡ ናቸው።
መንገድ ያስጀመረንን አንድነት ሊደቁሱ፣ እጅ ለእጅ ያስተሳሰረንን ገመድ ሊበጣጥሱ፣ የጋራ ቤታችንን ሊደረማምሱ የሚቋምጡ ብርቱ ፈተናዎቻች ጉዞ ከመጀመራችን በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ።
ምናልባትም መንገዳችን ላይ ልዩ ልዩ ጋሬጣዎችን እየጣሉ ከጉዟችን ሊያስቀሩን የሚሹ አካላትን ድብቅ ፍላጎት በአግባቡ ተረድተን በጥንቃቄና በጥበብ ወደ ግባችን መጓዛችንን እንደማናቆም እስካላሳየናቸው ድረስ በቀሪ ምዕራፎቻችንም ላይ ተከትለውን ይመጣሉ።
የጠላቶቻችን ፍላጎት በጉዞአችን መሐል ወድቀን ግባችንን ሳናሳካ እንድንቀር ነው። በጋራ ቆመን ያጸናነው ቤታችን ፈራርሶ ወደ ትቢያነት ሲቀየር ማየት ይሻሉ። እኛ ደግሞ ለዚያ የተመቸን ኾነንላቸዋል።
አንድ ቤት በሦስት ምክንያቶች ሊፈርስ ይችላል። በግንባታው ወቅት በገጠሙት ችግሮች፣ ከውስጥ ባሉ ሰዎች እና ከውጭ በሚመጡ ኃይሎች።
እነዚህ ሦስቱ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ የሚተባበሩበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ በዓላማ፣ አንዳንድ ጊዜ በሒደት፣ አንዳንድ ጊዜም በውጤት ይተባበራሉ። ከውስጥ ያሉት ሰዎች በውስጥ ጉዳያቸው ሲጣሉ፤ ከውጭ ያሉ ኃይሎች ቤቱን አፍርሰው ቤቱ የተገነባበትን ቦታ ወይም በቤቱ ውስጥ ያለውን ሀብት መዝረፍ ሲፈልጉ፣ ቤቱ እንዲፈርስ ተባብረው ሊሠሩ ይችላሉ።
ቤቱ ሲገነባ ያጋጠሙት ችግሮች ካሉ ደግሞ ነገሩ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ዐይነት ይኾናል።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን፣
ሁላችንም ልንዘነጋው የማይገባን አንድ ሐቅ አለ። አገራችን የጋራ ቤታችን ናት። የሁላችንም ቤቶች በዚያች ትልቅ ቤት ውስጥ የሚገኙ የቤቱ ክፍሎች ናቸው። በየክፍሎቻችን ተወሽቀን ያለነው ሁላችንም የጋራ ቤታችንን አጽንተን በማቆየት ላይ ተመሳሳይ አቅምና አቋም የለንም። ቤትን ከውጭ የሚመጣ ኃይል ብቻውን አያፈርሰውም። የውስጦቹ ካልተባበሩት በቀር።
የቤቱ ሰዎች የውጭ አፍራሾች በሦስት መንገድ ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሊተባበሯቸው ይችላሉ። ኾን ብለው፣ ሞኝ ኾነው እና ተኝተው።
ከሚፈርስ ቤት እንጠቀማለን የሚሉ ሞኝ የቤት ሰዎች አሉ። ከመሥራትና ከመድከም ዋጋ ማግኘት የሚከብዳቸው፤ የቤቱን ፍርስራሽ ሽጠው ማትረፍ የሚፈልጉ የፍርስራሽ ጌቶች አሉ። እነዚህ ኾን ብለው ቤቱ እንዲፈረስ ይሠራሉ። ቤቱ ቶሎ ፈራርሶላቸው ፍራሹን ለመቸብቸብ ስለሚቸኩሉ፣ ከውጭ ኾነው ቤቱን ከሚነቀንቁት ጋር ተባብረው ያፈርሳሉ።
ሌሎቹ ደግሞ በምግቡም፣ በልብሱም፣ በሳሎኑም በመኝታ ቤቱም የሚፈጠርባቸውን ቅሬታ የቤት ማፍረሻ ምክንያት የሚያደርጉ የዋሐን ባለቤቶች ናቸው። “የላሞች ጠብ በረቱን ለተኩላ፤ የውሾች ጠብ መንደሩን ለጅብ ይሰጠዋል” እንደሚባለው፣ እነዚህ የቤት ልጆች ከውጭ ያሰፈሰፈውን ጠላት ባለማወቅ የሚያደርጉት ጠብ፣ ከተራ እሰጥ አገባ አልፎ ሳያስቡት ቤቱን ያፈርሰዋል።
አንዴ ከፈረሰ በኋላ ለውስጦቹ ትርፋቸው ቁጭት ይኾናል። ከመኾኑ በፊት እንጂ ነገሮች ከተበለሻሹ በኋላ መጸጸትና መቆጨቱ ምንም ትርጉም የለውም።
ሦስተኞቹ ደግሞ ተኝተው ቤት የሚያፈርሱ ናቸው። የቆሸሸውን ማጽዳት፣ የተሰነጠቀውን መጠገን፣ የጎደለውን ማሟላት፤ የጠመመውን ማቅናት ሲገባቸው “እኔ ምን አገባኝ” ብለው ይተኛሉ። አጥሩ ሲፈርስ ሳሎን - ሲድረስ ይላሉ፤ ሳሎን ሲፈርስ - መኝታ ቤት እስኪደርስ ይጠብቃሉ፤ መኝታ ቤቱ ሲፈርስ ጓዳ ተደብቀው በመተኛታቸው የሚተርፉ ይመስላቸዋል። ሁሉም ግን የጊዜ ጉዳይ ይኾናል።
ዛሬ ታላቋ ቤታችን ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ናት። ሦስቱም ዐይነት ልጆች አሏት። ከውጭ ጠላቶቿ ጋር ይሁነኝ ብለው በዓላማ ለማፍረስ የሚሠሩ፤ በዓላማ ባይገጥሙም በውጤት ከውጭ አፍራሾች ጋር የሚሠሩ፤ ቤታቸው ሲቃጠል እያዩ ከመንቃት ይልቅ በሙቀቱ ተከናንበው የተኙ።
ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ከወሳኝ ወቅቶች አንዱ ነው። በአንድ በኩል ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ምርጫ አድርገን በሕዝብ ድምፅ የሚጸና መንግሥት ለመመሥረት በሒደት ላይ ነን።
በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችን ከፍታ አንዱ ማሳያ የኾነውን የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ለማከናወን እየተጋን ነው። ከእነዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ግሥጋሴ ከሚያሠጋቸው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጋር በየአቅጣጫው ግንባር ለግንባር ገጥመናል።
ኢትዮጵያ እነዚህን ሦስት ፈተናዎች አልፋ ግቦቿን ካሳካች፣ ከዚያ በኋላ ለማንም በቀላሉ እጅ የማትሰጥ የሁላችን መመኪያ ሆናትወጣለች።
ይህ እንዳይሳካ “ከምንጩ እናደፍርሰው፣ ከእንጎቻው እንሰቅስቀው፣ ከእሸቱ እናጠውልገው” የሚሉ የማሰናከያ ድንጋዮች በየአቅጣጫው ተነሥተዋል። ወሳኙ የእነርሱ መነሣት አይደለም፤ የእኛ ምላሽ እንጂ።
ውድ የአገራችን ሕዝቦች፣ ከለውጡ ጅማሬ አንሥቶ የገዛ ዛፋችንን ከዛፉ በተቆረጠ ጠማማ እንጨት የመቁረጥ አዝማሚያ መኖሩን እየተናገርንም፣ እየታገልንም ነበር። በተለያየ አቅጣጫ የሚወረወረው ድንጋት በቤታችን ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመግታት፣ የፖለቲካ አመራሩና የጸጥታ አካሉ መሥዋዕትነት የተከፈለበት ትግል አካሒዷል። ከጁንታው ጋር የተደረገው ትግል የዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
እነዚህ አካላት ዛሬም አልጠፉም። የተለያዩ ብሔሮችን ስሞች ይዘው፣ ሲመች በሰላም፤ ሳይመች በጠመንጃ የላኪዎቻቸውን ዓላማ ለማሳካት እየሠሩ ነው። የእነዚህን ተልዕኮ ያልተረዱ የዋሖች ደግሞ አገር እንድትፈርስ ባይፈልጉም አገር እንድትፈርስ ግን እየሠሩ ነው።
የቤቱ ጥያቄ የሚመለሰው መጀመሪያ ቤቱ ሲኖር መኾኑን ዘንግተውታል። ቤት እያፈረሱ ስለ ቤት ለመወያት ይፈልጋሉ። “ቤቴን እጠብቃለሁ፤ ሙግቴንም እሟገታለሁ” የሚሉ አባቶች ልጆች መኾናቸውን ረስተውታል። ስለ ላሟ ወተት የሚኖረው ጥያቄ የሚመለሰው መጀመሪያ ላሟ ስትኖር መኾኑን ረስተውታል። ከእነዚህ ከሁለቱ ጋር ተደምረው “ምን አገባኝ” የሚሉ ዜጎችም አሉ።
ምድር ቤቱ ሲቃጠል እሳቱ ሰባተኛ ፎቅ ላይ የሚደርስ የማይመስላቸው። ወይ ለመገንባት ወይ ለመመከት አንዳች የማያደርጉ፡፡ እሳቱን ከመከላከል ይልቅ በሙቀቱ ተመቻችተው ያንቀላፉት ጭምር የአገራችን ችግሮች ናቸው።
አሁን በአለንበት ጊዜ ሦስት ወሳኝ ዓላማዎቻችንን በጽናት ማሳካት ይኖርብናል። በመጀመሪያ አንድ ወር ያህል ጊዜ የቀረውን ምርጫ ውጤታማ እናድርገው። በነቂስ ወጥተን ካርድ እንውሰድ። ሁላችንም ይበጀናል ያልነውን እንምረጥ።
የፈለግነውን እንዳንመርጥ እንቅፋት የሚኾንብን የትኛውም አካል እርሱ የኢትዮጵያ ጠላት ነው። የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እየተቋቋምን፤ ችግሮችን እያረምን፣ ጉድለቶችን እየሞላን ምርጫውን ውጤታማ እናድርገው። ይሔንን ምርጫ በድል ተወጣነው የምንለው ሒደቱ የሚጠበቅበትን ደረጃ ለማለፍ ከቻለ ነው። ለዚህ ደግሞ መራጩ ሕዝብ፣ ተመራጮች እና የምርጫ ቦርድ አገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን።
ሁለተኛ ከምርጫው ጎን ለጎን ግድባችንን ባቀድነው መንገድና ጊዜ መገንባትና ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን አለብን።
የትኛውንም ዐይነት ጫና ተቋቁመን፤ የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን አልፈን እንሞላዋለን። ኢትዮጵያን መውደዳችንን የምናሳየው የኢትዮጵያን ጉዞ በማቀላጠፍ እንጂ በማደናቀፍ አይደለም። በእሳት ላንቃ ውስጥ እያለፍንም ቢኾን ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን። በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን።
በየአቅጣጫው የምናየው የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ቤትና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በአገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም። አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተመርቶ በአገር ውስጥ የሚገጣጠም ጥፋት ነው። ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙት የእፉኝት ልጆች ናቸው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ የእፉኝቶችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል።
ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና እዚያ የጣላቸው ግልገሎቹ ግን አሁንም ይቀራሉ። የትኛውንም ዐይነት የብሔርና የእምነት ስም ቢይዙ፤ ከየትኛው የውጭ ኃይል የሚረዱትን ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይኾናል እንጂ አያሸንፏትም።
መጀመሪያ በውስጣችን ያሉትን ባለ ሁለት ቢላዋዎች እናጸዳለን። ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ አሉ። እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ዋነኞቹ ጠላቶቻችን ናቸው። አጥር ላይ ተቀምጠው፣ አሸናፊውን ዓይተው፣ ከተመቻቸው ሊገቡ፣ ካልተመቻቸው ሊሸሹ የሚያስቡ መኖራቸውን ዐውቀናል። ወቅቱ የምርጫ ነውና መምረጥ አለብን። ወይ እነርሱን እናጸዳለን ወይ ኢትዮጵያን አሳልፈን እንሰጣለን። የኛ ምርጫ ኢትዮጵያን ለእነርሱ ስንል መሠዋት ሳይኾን፤ እነርሱን ለኢትዮጵያ ስንል መሠዋት ነው።
በአጠቃላይ ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ፤ ግድባችንን በታቀደለት መንገድ ገንብተን ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማከናወን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ታድገን ወደሚገባት ደረጃ ለመውሰድ እንድንችል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃትና በብስለት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። ቆም ብለን እናስብ፤ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም።
በፌዴራልና በክልል የምትገኙ የጸጥታ አካላት፣ ተቀናጅታችሁና ተናብባችሁ በመሥራት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያን ሰላምና ደኅንነት እንድታስጠብቁ እናሳስባለን።
የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካና የመብት እንቅስቃሴዎች ይደገፋሉ። የትግላችን ውጤቶች ናቸውና። እነዚህ የመብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ግን ኢትዮጵያን እንዲያናውጡ አንፈቅድም። ፖለቲካዊ ጨዋታውን ከጨዋታ ሜዳ ውጭ ለማድረግ ለሚፈልጉት ኃይሎች፣ ትዕግሥታችን ማለቁን በዚሁ አጋጣሚ ልንነግራቸው እንፈልጋለን።
ሁሌም እንደምንለው፤ በጽናትም እንደምናምንበት፣ ለኢትዮጵያ ፈተና ብርቋ፣ ድል ማድረግም ሰበር ዜናዋ አይደለም። ከዚህ በላይ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች።
ይሔንን አልፋ ነገ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ማሸነፏ ላይቀር እንዳታሸንፍ ሲታገሉ የኖሩትን ትታዘባቸዋለች፤ በታሪክ ሒደትም ትቀጣቸዋለች። እርሷ ግን ወጥመዱን በጣጥሳ፣ ሰንኮፉን ነቃቅላ፣ አዚሙን አስወግዳ ያሰበችበት ትደርሳለች።
ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችውም ወደፊትም የምትቆየውም፣ በእኛ በመሥዕዋት ልጆቿ ደምና አጥንት ነው። ዛሬ እኛ የምንከፍለው ዋጋ፣ ነገና ከነገ ወዲያ አገራችንን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ከፍታ ላይ እንደሚያደርሳት ምንም ጥርጥር የለውም።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት
ሚያዝያ 16፣ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ



