ከ186 ሺህ በላይ ገጀራ በሕገወጥ መንገድ ገብቶ፤ ቀረጥ ተከፍሎበት ከተለቀቀ በኋላ ተያዘ
በተጭበረበረ ሰነድ አገር ውስጥ በአራት ኮንቴነሮች የገባውና 186,240 የሚኾኑ ገጀራዎች ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥ ተከፍሎባቸው ከተለቀቁ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለዋል
ከ186 ሺህ በላይ የሚኾኑ ገጀራዎች በተጭበረበረ መንገድ የገቡ ናቸው ተብሏል
በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ጉምሩክ እንዲለቀቅ ፈቅዶ ነበር
ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 26, 2021)፦ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እንደ አገር እየተፈተነ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት በተጭበረበረ ሰነድ ወደ አገር ውስጥ የገባና በአራት ኮንቴነሮች የተጫነ ከ186 ሺህ በላይ ገጀራዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሐሰተኛ ሰነድ ተጠቅሞ ሞጆ ደረቅ ወደብ የደረሰው ይህ ገጀራ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፍቃድ የተሰጠው ስለመኾኑ ሰነድ የቀረበበት ቢኾንም፤ ይህ ሰነድ ሲጣራ ግን ሐሰተኛ መኾኑ ሊረጋገጥ በመቻሉ መያዙ ታውቋል።
ይህ በተጭበረበረ መንገድ ወደ አገር ገብቶ በቀረበው ሰነድ መሠረት ከ7.7 (ከሰባት ነጥብ ሰባት) ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥ ተከፍሎበት ይህ ከ186 ሺህ በላይ የሚኾን ገጀራ እንዲለቀቅ ተፈቅዶለት እንደነበር የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ይፋ የተደረገው የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ከፌዴራል ወንጀል መከላከያ ጋር በተደረገ ማጣራት ሐሰተኛ ሰነድ ተጠቅሞና ከፌዴራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው ዳዊት የማነ አስመጪ እንደኾነ ይጠቅሳል።
ድርጊቱ ከ15 ቀን በፊት ስለመፈጸሙ የሚጠቅሰው ይኸው የገቢዎች መረጃ፤ 186,240 የሚኾኑ ገጀራዎች በአራት ኮንቴነሮች የገቡት፤ ከፖሊስም እንዲገቡ ፍቃድ ያላገኙ ናቸው።
አያይዞም ድርጊቱ ከ15 ቀን በፊት የተፈጸመ እንደነበር በማስታወስ፤ በወቅቱ አስመጪው ያቀረቡት ሰነድ ሕጋዊ ነው በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር ሲጣራ ቆይቶ የተገኘው ውጤት የቀረበው ሰነድ ሐሰተኛ መኾኑን ማረጋገጥ ተችሏል።
አስመጪው ከፌዴራል ፍቃድ ተሰጥቶኛል ብለው ያቀረቡት ሰነድ ያልተሰጣቸው እንደኾነም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
ገጀራዎቹ ቀረጥ ተከፍሎባቸው ተለቀው እንደነበር ከሚገልጽበት የዛሬው የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ፤ በጉምሩክ ኮምሽን ሠራተኛ የእጅ ገጀራው ተገቢውን የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት በመፈጸም እንዲስተናገድ የሚገልጽ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት እንደኾነ ገልጿል።
በዚሁ መነሻነት በፌዴራል ፖሊስ ለሞጆ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መረጃውን በመስጠት ክትትል ተደርጐ የዕቃው ባለቤትና ትራንዚተሩ ተይዘው በምርመራ ላይ ስለመኾናቸው ገልጿል።
በአገሪቱ ሕግ መሠረት ክልከላ ከተደረገባቸውና ከፌዴራል ፖሊስ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይሰጣቸው መግባት ከማይችሉ ዕቃዎች መካከል አንዱ የኾነው ገጀራ፤ ከቻይና ተጭኖ ሞጆ ጉምሩክ የደረሰ ነው።
በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-1919/21 ተመዝግቦ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደ ለማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ የቀረበበት ቢኾንም፤ የቀረበውን ሰነድ የገቢዎች ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው ተመርምሮ ከ7.7 ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት ዕቃው ተለቅቆ እንደነበር ከገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ መገንዘብ ይቻላል።
ገጀራው ከተለቀቀ በኋላ ግን በጉምሩክ ኮምሽንና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጐ፤ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛ እና ዕቃውን ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መኾኑን ማረጋገጥ ከተቻለ በኋላ ገጀራው ሊያዝ ስለመቻሉ የሚጠቁም ነው።
ይህ ዘገባ ብዥታ ያለበት ነው የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ሲሆን፤ በተለይ ገጀራው በሐሰተኛ መረጃም ቢኾን የጉምሩክ ቀረጥ ተከፍሎበት እንዲለቀቅ ከተደረገ በኋላ፤ ከጉምሩክ የወጣ ኮንቴነር አለ የሚለውን አመለካከት እንዲያጭር አድርጓል።
ገቢዎች ከጉምሩክ እንዲለቀቅ ውሳኔ አስተላልፏልና ገጀራ የያዙት አራቱም ኮንቴነሮች ሳይወጡ መያዛቸውን ወይም ከአራቱ ኮንቴነሮች ውስጥ የወጣ መኖር አለመኖሩም አለመጥቀሱ ሌላው ጥያቄ የሚነሳበት ኾኗል።
ይህ በልዩ ፍቃድ መግባት ያለበትና ቢሠራጭ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትለው ቁጥሩ የበዛ ገጀራ ለምን በተጭበረበረ ሰነድ እንዲገባ ተፈለገ የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ ኾኗል።
ገቢዎች በዚህ ጉዳይ ላይ በመረጃው መጨረሻ ላይ ደግሞ፤ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ገፆች በጉምሩክ ኮምሽን ባለሙያ ዕቃው እንዲወጣ የተፈቀደበት ደብዳቤ በማስመሰልና ሐሰተኛ የደብዳቤ ፎቶ በመጠቀም አስመጪው ሕጋዊ እንደኾነ ተደርጐ የሚሠራጨው መረጃ ሐሰተኛ መኾኑን እወቁልኝ ብሏል። (ኢዛ)



