በአዲስ አበባ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ሲያትሙ የነበሩ ስምንት የውጭ ዜጎች ተያዙ
በቁጥጥር ሥር የዋሉት ኖቶች፣ መሣሪያዎችና ኬሚካሎች
ያትሙባቸው የነበሩ መሣሪያዎቻቸውም በቁጥጥር ሥር ውለዋል
ኢዛ (ቅዳሜ ኅዳር ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 16, 2019)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ተከራይተው ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ሲያትሙ የነበሩ ስምንት የውጭ ዜቶችን ሕገወጥ ገንዘብ ያትሙባቸው ከነበሩ መሣሪያዎቻቸው ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ትናንት ኅዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የአዲስ አበባ ፖሊስ በቅንጅት ባደረጉት ክትትል ሐሰተኛ ገንዘብ አታሚ የውጭ ዜጎች ሕገወጥ ተግባሩን ይፈጽሙ የነበረው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት በተከራዩዋቸው ሁለት መኖሪያ ቤቶች ነው።
በመኖሪያ ቤቱም ሐሰተኛ ገንዘብ የሚታተምባቸው ልዩ ልዩ መሣሪያዎች፣ በሕገወጥ መንገድ ያዘጋጁዋቸው 512 ሐሰተኛ ዶላር ተይዟል። እንዲሁም ትክክለኛ የኾኑ 455 ሺህ 200 ብርና 1900 ዶላር ተይዟል። ከዚህም ሌላ ሐሰተኛ ዶላርና የኢትዮጵያ ብር ለማተም የተዘጋጁ ብዛት ያላቸው ወረቀቶችንና ኬሚካሎችን ስለመያዙም ፖሊስ አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።
ፖሊስ የተያዙት እነዚህ ስምንት የውጭ ዜግነት አላቸው የተባሉ ተጥርጣሪዎች የየት አገር ዜጎች እንደኾኑ አልጠቀሰም። (ኢዛ)



