Oromo Federalist Congress (OFC)

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)

የመራጮች ምዝገባ ከሚጠበቀው በታች መኾኑን ጠቅሶ፤ ምርጫው የይስሙላ ነው ሲል ኦፌኮ ተችቷል

ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 29, 2021)፦ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ለመካሔድ አምስት ሳምንታት ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅት፤ ምርጫው ቀርቶ የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ይመቻች ሲል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዛሬ ይፋ በወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ፓርቲው “ከብሔራዊ መግባባት መሸሽ የአገራችንን ችግሮች እያባባሰና እያወሳሰበ ነው” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሁሉንም አቀፍ ያልኾነ ምርጫ ለማካሔድ መጣደፉን አቁመው፤ የብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲያመቻቹ ጠይቋል።

ፓርቲው ገጠመኝ ያላቸውንም ችግሮች ባካተተበት እና በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በዛሬው ዕለት ባሰራጨው መግለጫው፤ አባሎቼ ላይ ደረሰ ያላቸውንም አካትቷል።

ምርጫውን በተመለከተም እንደገለጸው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች በቂ መራጮች ያለመመዝገባቸውን በመግለጽ፤ ምርጫው የይስሙላ ስለመኾኑም ጠቅሷል።

ኦፌኮ ከዚህ ቀደምም በብሔራዊ መግባባት ላይ ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረበ መኾኑ የሚታወስ ነው። ፓርቲው በመግለጫው ላይ ስለወቅታዊው የምርጫ ጉዳይ ይጥቀስ እንጂ፤ በዘንድሮው ምርጫ እንደማይሳተፍ ይታወቃል። የፓርቲው የዛሬው መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከብሔራዊ መግባባት መሸሽ ያገራችንን ችግሮች እያባባሰና እያወሳሰበ ነው

ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ

ዛሬ አገራችን በቀውስ እየተናጠች ነው፤ ሰላም የለም። የአገራችን አንዳንድ ክፍሎች ኮማንድ ፖስት ሥር ይተዳደራሉ። የሕግ የበላይነት እየተከበረ አይደለም። ፍርድ ቤት በነፃ ወይም በዋስ የለቀቀውን ፖሊስ ያስራል። የበለጠ በጣም አሳሳቢው ደግሞ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጎች በማን አለብኝነት ከእስር ቤት እያወጡ ያለፍርድ መግደል የተለመደ ኾኗል። የሆሮ ጉዱሩ ዞን ጂማ ራሬ ወረዳ ነዋሪዎች፤ ባኔ ነገሪ፣ ብርሃኑ ቶለሳ፣ በላይ ጢቂ፣ ጉታ ጫራና፣ ጭምዴሳ ሶቾሳ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። በሌሎች የኦሮምያ አከባቢዎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።

የአገሪቱ ዋና ከተማና አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎችን አንድም ጨርሶ አያገኙም፤ ወይም በበቂ ሁኔታ አያገኙም ወይም ሊከፍሉት ከሚችሉት ዋጋ በላይ ይጠየቃሉ። ይህ ሁሉ ሊኾን የቻለው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሕወሓት/ኢሕአዴግ በመቀጠልም የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲያደርሱ ከቆዩት የመልካም አስተዳደር ጉደለት የተነሳ መኾኑ በማንም የማይታበል ሐቅ ነው።

ፓርቲያችን ኦፌኮ የአገሪቱ ውስብስብ ችግሮች በብሔራዊ መግባባት ይፈቱ ዘንድ ያደረጋቸው እጅግ ብዛት ያላቸው ጥሪዎች እየተድበሰበሱ በመታለፉቸው፤ አገራችን ልትወጣ ከማትችልበት ሁለንትናዊ መመሰቃቀል ውስጥ ገብታ ትገኛለች። በአማራ ክልል በኦሮሞ ልዩ ዞን ውስጥ በሕዝብና በመንግሥት ልዩ ኃይል መኻል ሕይወት የጠፋበትና ንብረት የወደመበት እጅግ በጣም ዘግናኝ ግጭት ተከስቷል። እንዲያውም የኦሮሞ ብሔር ሕዝብን ከኢትዮጵያ በመነጠል ለማንም በማይጠቅም መልኩ “ኦሮሙማ ይውደም! ኢትዮጵያ ትቅድም!” የሚል መፈክር በአማራ ከተሞች በአደባባይ ተስተጋብቷል። በበኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕዝብን ያፈናቀለ፣ ሕይወትን ያጠፋና ንብረትን ያወደመ ግጭት ተፈጥሯል። በኦሮምያ ክልል በወለጋና ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች ግጭት በመስፋፋቱ ብዙ ሕይወት እየጠፋ ነው። ትግራይ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ቀውስ ከኛ አልፎ የዓለም መነጋገሪያ ኾኗል። እነዚህና ሌሎች ችግሮች እያሉ መንግሥት በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበና በኛ እምነት ችግሮችን ያባብስ እንደኾነ እንጂ፤ ችግሮችን የማይፈታ ምርጫ እንዲካሔድ እየገፋ ነው። ኦፌኮ በገዥው ፓርቲ ጫና ከምርጫ ውድድሩ የወጣ ቢኾንም፤ በኃይል ምርጫን ለማስፈጸም ከመሯሯጥ አስቀድሞ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚመረጥ አሁን አጥብቀን እንመክራለን።

አንጻራዊ ሰላም ይታይባታል ከምትባለው ርዕሰ ከተማ ፊንፊኔ/አዲስ አበባን ጨምሮ የመራጮች ምዝገባ ከሚጠበቀው በታች መኾኑ ምርጫው የሕዝቡን ስሜት አለመሳቡን በግልጽ ያመለክታል። ይህ የምርጫ ቲያትር ዘመን እንዳለፈም የሚያሳይ ምልክት ነው ብለን እናምናለን። ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ዘመን ነው። ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል። ከእርዳታ ሰጪና አበዳሪ አገሮች ጋር አገራችን እየገባችበት ያለው አለመግባባት ኋላ ላይ ውድ ዋጋ ሊያስከፍላት የሚችል ይመስለናል። ዜጎች ቢያንስ የትራንስፖርትና የመሠረታዊ አቅርቦት አገልግሎት ከማያገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰው የከተማ ውስጥ ዘራፊዎች መጫወቻ እስከመኾን ደርሰዋል። ከነዚህ አስከፊ ችግሮች ለመላቀቅ መፍትሔ መሻት ይኼን ያህል ቀላል ይኾናል ተብሎ ባይገመትም፤ መንግሥት ከብሔራዊ መግባባት መሸሹ ሕዝባችንን ለበጠ አደጋ ከማጋለጥ የበለጠ ፋይዳ ያለው አይመስለንም።

ስለኾነም፤ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሁሉንም አቀፍ ያልኾነ ምርጫ ከማካሔድ መጣደፉን አቁመው፤ የእርቅና ብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲያመቻቹና አገራችን ከተጋረጠባት መመሰቃቀል እንዲትወጣ እንዲያደርጉ አበክረን እየጠየቅን፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአገሪቱ ዴሞክራሲ ኃይሎችና የዓለም ማኅበረሰብ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እንድወጣ የየበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ